ኮቪድ-19፡ የኮሮናቫይረስ ክትባቶች ቅይጥ ቫይረሱን በጥሩ መንገድ መከላከል እንደሚችል ጥናት አመለከተ

ታትሟል

ለመጀመሪያውም ይሁን ለሁለተኛው ዙር የኮሮናቫይረስ ክትባት የተለያዩ ምርቶችን ቀላቅሎ መጠቀም ቫይረሱን በሚገባ መከላከል እንደሚችል በዩናይትድ ኪንግደም የተደረገ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

የፋይዘርና የአስትራዜኒካ ክትባቶችን በተለያየ ቅደም ተከተል በመስጠት የተደረገው ሙከራ ውጤታማ ነው ተብሏል።

በሁለቱም ቅደም ተከተል የተደረገው ሙከራ በጥሩ ሁኔታ ሰርቷል የተባለ ሲሆን በሽታ የመከላከል ሥርዓትን ማሻሻላቸውም ተጠቅሷል፡፡

ታዲያ ይህ ግኝት አዳዲስ የክትባት አይነቶች እንዲመረቱ በር የሚከፍት መሆኑን ባለሙያዎች አስረድተዋል።

የሙከራ ውጤቱም ቀደም ሲል ሁለት ዙር የአስትራዜኒካ ክትባት በክረምት ወቅት የወሰዱ ሰዎች ተጨማሪ ክትባት ቢወስዱ ጠንካራ የመከላከል አቅማቸውን ሊያዳብሩ እንደሚችሉ ፍንጭ ተሰጥቷል፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም የታወቁት የሕክምና ባለሙያ ፕሮፌሰር ጆናታን ቫንታም በዩኬ ውስጥ አሁን እየተሰጠ ያለውንና ውጤታማ የሆነውን ተመሳሳይ [ያልተቀላቀለ] ክትባትን የማዳረስ መርሃ ግብርን ለመለወጥ ምንም ምክንያት የለም ያሉ ሲሆን፤ ክትባቶቹ በጥሩ አቅርቦት ላይ ያሉ እና ሕይወትን የሚያድኑ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ሆኖም ለወደፊቱ አንዳች ነገር ለሆን ይችላል የሚሉት ፕሮፌሰሩ "ክትባቶቹን ቀይጦ መጠቀም መርሃ ግብሩን የበለጠ እንደጊዜው ለማስኬድ እንዲሁም የክትባት ምርት ሂደት ላይ ያሉ አገራትን ለመደገፍ እና የክትባት አቅርቦት ችግር ያጋጠማቸው አገራትን ለመርዳት ይግዛል" ብለዋል።

የተለያዩ አገራት ክትባቶችን ቀላቅለው መጠቀም ጀምረዋል።

ስፔን እና ጀርመን የአስትራዜኔካ የመጀመሪያ ዙር ክትባት ለወሰዱ ታዳጊዎች ፋይዘር ወይም ሞዴርና የተሰኙ ክትባቶችን ለሁለተኛ ዙር እየሰጡ ነው።

ይሁን እንጅ ክትባቶችን ቀላቅለው የወሰዱ ሰዎች አልፎ አልፎ የደም መርጋት ችግርን እንዳጋጠማቸው ተገልጿል።