ምርጫ 2013፡ በደሴ እና በሐዋሳ የኢዜማ ተወካዮች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ 'ቅሬታቸውን' ገለጹ

በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ኢዜማ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ችግሮች አሉ ሲል ቅሬታውን አሰምቷል።
በሐዋሳ ከተማ ኢዜማን ወክለው ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩት ወንድማገኝ ባርገና ሐዋሳ ሐይቅ አካባቢ ወደ ሚገኘው የምርጫ ጣቢያ ሲሄዱ ያገኟቸው የኢዜማ ፓርቲ ምርጫ ታዛቢዎችን እንደማያውቋቸው ይናገራሉ።
በሌላ በኩል በየም ልዩ ወረዳ ኢዜማን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየተወዳደሩ የሚገኙት አቶ አሰፋ ወንድሙ የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ ታዛቢዎች "የእኛ አይደሉም" ይላሉ።
አቶ አሰፋ አክለው የገዢው ፓርቲ አባላትና የፀጥታ ኃይሎች "ብልጽግናን ካልመረጣችሁ እያሉ ሕዝቡን እያስፈራሩ ነው" ባይ ናቸው።
የኢዜማ ቃል አቀባይ የሆኑት ናትናኤል ፈለቀ ከጉራጌ ዞን ቅሬታ እንደደረሳቸው ጠቁመው በሐዋሳ ስላለው ጉዳይ ግን እንደማያውቁ ይናገራሉ።
ቃል አቀባይ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
"የማናውቃቸው ምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተዋል"
በደሴ ከተማ የኢዜማ ተወካይ የሆኑት ግለሰብ በበኩላቸው የማናውቃቸው የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው አግኝተናል ሲሉ ገልፀዋል።
በደሴ ምርጫ ክልል ኢዜማን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች የሚወዳደሩት አቶ መንግሥቱ አመዴ "በአንዳንድ የምርጫ አካባቢዎች የማናውቃቸው የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው አግኝተናል" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አቶ መንግሥቱ "በአንዳንድ ቦታዎች አንድ ምርጫ ጣቢያ የነበረው ሁለት ሆኖ፤ ሦስት የነበረው አንድ ጣቢያ ሆኖ አግኝተናል" ብለዋል። ይህም ለታዛቢዎችም ለመራጮችም አደናጋሪ ሆኗል፤ አዲስ በተከፈቱ ጣቢያዎች ታዛቢያችንን እንዳንልክ ሆነናል" ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የቃለ ጉባኤ መዝገብ የሌለበትም ጣቢያ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
እንደ እርሳቸው ከሆነ የቃለ ጉባኤ መዝገብ ታዛቢዎችና ምርጫ አስፈጻሚዎች የምርጫ ሒደቱንና ውጤቱን መዝግበው ይዘው መጨረሻ ላይ የሚፈራረሙበት መዝገብ ነው።
በሌላም በኩል በቂ ታዛቢዎች አለመገኘትና በሌላ የቀበሌ አመራርና እድርተኞች ለመሸፈን የመሞከር አሰራሮችን መመልከታቸውን አክለዋል።
በአንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች የቅሬታ ሰሚዎች አለመገኘትም አቶ መንግሥቱ የተናገሩት ሌላኛው ቅሬታ ነው።
ክፍተቶች ታይተውባቸዋል ካሉት የምርጫ ጣቢያዎች መካከል ሰኞ ገበያ፣ ሳላይሽና ፒያሳ ምርጫ ጣቢያ ይገኙበታል።
አቶ መንግሥቱ ይህንን ችግር ለከተማው ምርጫ ክልል አስፈጻሚ ለማሳወቅ ሞክረው ኃላፊው ስልክ ባለማንሳታቸው ይህንንን ማድረግ አልቻልንም ብለዋል።
ቢቢሲም የደሴ ምርጫ ክልል ኃላፊ አቶ ዮሐንስ አሰፋን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ስልካቸው ዝግ በመሆኑ አልተሳካም።
ስድስተኛውን ምርጫ በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ብርቱካን ሚደቅሳ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅሬታ ለቦርዱ እያቀረቡ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ብርቱካን ከገዥው ፓርቲ በስተቀር አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች በተለይ ደግሞ በአማራ ክልል የሚገኙ ተወዳዳሪዎች ቅሬታቸውን እንዳሰሙ ተናግረዋል።
ሊቀመንበሯ የመንግሥት ሹመኞችና የፀጥታ አካላት በመራጩ ሕዝብ ላይ ጫና ከማድረስ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል እየተካሄደ ይገኛል። በአንዳንድ ክልሎችና በተወሰኑ አካባቢዎች በፀጥታና በሌሎች ምክንያቶች ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ሆኗል።













