ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተመድ በሚየንማር ወታደራዊ አገዛዝ ላይ የጦር መሳሪያ ሽያጭ እቀባ ጥሪ አደረገ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባልተለመደ ሁኔታ ለሚየንማር ወታደራዊ አገዛዝ የጦር መሳሪያ ሸያጭ እንዲቆም ጥሪ አድርጓል።
የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ በየካቲት ወር የተመረጠውን የሚየንማር መንግሥት በኃይል በመጣሉም ጦሩን የሚያወግዝ ውሳኔን አሳልፏል።
ተመድ ተመራጯ መሪ አን ሳን ሱቺን ጨምሮ በእስር ላይ ያሉ ፖለቲከኞች እንዲለቀቁ እንዲሁም በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል።
ተመድ በዚህ ወቅትም ሪዞሉሽን ያሳለፈ ሲሆን በርካታ ነገሮችን ሊቀይርም ይችላል ተብሏል።
"ከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ሊከሰት እንደሚችልም ጠቋሚ ነገሮች አሉ" በማለት በሚየንማር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዑክ ክርስቲን ሽራነር በርግነር ለጠቅላላ ጉባኤው ተናግረዋል።
"በአሁኑ ወቅት የወታደራዊውን ኃይል ስልጣኑን ወደ ሰላማዊ መንግሥት የመመለሻ ጊዜው እየጠበበ ነው" ብለዋል።
ውሳኔውን 119 አገራት የደገፉት ሲሆን ቤላሩስ በብቸኝነት ተቃውማዋለች።
ለሚየንማር የጦር መሳሪያ በአብዛኛው የሚሰጡት ቻይናና ሩሲያን ጨምሮ 36 አገራት በድምፀ ተአቅቦ ውሳኔው ተላልፏል።
ድምፀ ተአቅቦ ያደረጉት አንዳንድ አገራት ይህ ሁኔታ የሚየንማር የውስጥ ጉዳይ ነው ያሉ ሲሆን ሌሎች አገራት ደግሞ በሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ ስለደረሰው ጭፍጨፋ ውሳኔው ምንም ባለማለቱ ነው ድምፅ አንሰጥም ያሉት።
በሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ በደረሰ ጥቃት አንድ ሚሊየን የሚሆኑት አገራቸውን ለቀው ተሰደዋል።
በአውሮፓ ህብረት የተመድ አምባሳደር የሆኑት ኦሎፍ ስኩግ ውሳኔው "ወታደራዊውን ኃይል ህገ ወጥ አድርጎታል። በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃትና ጭካኔን አውግዟል። ከዚህም በተጨማሪ በአለም ዘንድ እንዲገለለልም ያደርጋል" ብለዋል።
በተመድ የሚየንማር የተመራጩ መንግሥት አምባሳደር የሆኑት ክያው ሞ ቱን ጠቅላላ ጉባኤው ይህንን "የደከመ" ውሳኔ ለማስተላለፍ ይህንን ያህል ጊዜ መውሰዱ አሳዛኝ ነው ብለውታል።
የአን ሳን ሱቺ ፓርቲ ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ ፓርቲ በከፍተኛ ድምፅ አሸንፎ መንግሥት መመስረት የቻለ ሲሆን ጦሩ በበኩሉ ተጭበርብሯል ከማለት አልፎ ለመፈንቅለ መንግሥቱንም እንደ ምክንያትነት ያቀርበዋል።
በቅርቡም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሚየንማር መፈንቅለ መንግሥት አመራሮች ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችላቸውን ትእዛዝ አስተላልፈዋል።
ጆ ባይደን ያሳለፉት እቀባ የጦሩ አመራሮች፣ ቤተሰቦቻቸውና ከነሱ ጋር የንግድ ሽርኪያ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉት ሁሉ ላይ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በአሜሪካ ተቀማጭ የሆነ የሚየንማር 1 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ጦሩ እንዳያገኘው ለማድረግ እግድ ለመጣል በሂደት ላይ ነው ተብሏል።
ጆ ባይደን መፈንቅለ መንግሥቱ እንዲቀለበስና መሪዋን አንግ ሳን ሱቺን ጨምሮ በእስር ላይ ያሉት የሲቪል አመራሮች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።