ከመቅደላ በዝርፊያ ወደ እንግሊዝ የተወሰዱ ቅርሶች በጨረታ እንዳይሸጡ ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Embassy of Ethiopia in london
እንግሊዝ ውስጥ በዛሬው ዕለት ሰኔ 10/2013 ዓ.ም በጨረታ ሊሸጡ የነበሩና ከመቅደላ የተዘረፉ ሁለት ቅርሶች ሽያጭ መቆሙ ተገለጸ።
ጨረታውን ያወጣው የእንግሊዙ በስቢ ኦክሽነርስና ቫሉወርስ የተባለ የጨረታ ድርጅት ሲሆን በእንግሊዝ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከድርጅቱ ኃላፊዎች ጋር ያደረገው ውይይትን ተከትሎ ነው ጨረታው እንዲንዲቋረጥ የተደረገው።
የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ በጨረታ ሊሸጡ የነበሩት ቅርሶች ጥንታዊ መጽሐፍ ቅዱስ ከነ ማኅደሩና መስቀል እንዲሁም ፅዋዎች መሆናቸውን አስታውቋል።
እነዚህ ቅርሶች በመቅደላ ጦርነት ወቅት ዘምተው ከነበሩት የእንግሊዝ ወታደሮች መካከል በጄኔራል ዊልያም አርቡትኖት አማካኝነት የተዘረፉ ናቸው።
በመቅደላ ወቅት የተዘረፉ ቅርሶችን ለማስመለስ እየተደረገ ካለው ጥረት ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለበስቢ ይፋዊ በሆነ ደብዳቤ ቅርሶቹ ከሽያጩ እንዲወጡ የጠየቀው ባለፈው ሳምነት ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ቅርሶቹንም ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱበትን ሁኔታ ድርጅቱ እንዲተባበርም ተጠይቋል።
"ከበስቢ ጋር ስምምነት ላይ በመድረሳችን ደስተኞች ነን። እነዚህ ቅርሶች ለኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ባህላዊ፣ መንፈሳዊና ታሪካዊ እሴቶች አሏቸው። የአሁኑም ሆነ መጪው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ቅርሶቻቸውን እንዲጠበቁ ይሻሉ። እናም እነዚህ ብርቅዬ ቅርሶች ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ወቅትም በጉጉት እንጠብቃለን" በማለት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል አቶ በየነ ገብረ መስቀል ተናግረዋል።
ኤምባሲው ቅርሶቹ ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱበትን ሁኔታም በተመለከተ ከበስቢ ጋርም ውይይቱን እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
የእንግሊዝ ሠራዊት ቅርሶቹን ከመቅደላ ለመውሰድ 15 ዝሆኖችንና 200 በቅሎዎችን ለማጓጓዣነት ተጠቅሞ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
በ2008 ኢትዮጵያ ከመቅደላ የተዘረፉና በሚሊዮን ዶላር የሚገመቱ ቅርሶቿ እንዲመለሱላት ለተለያዩ የእንግሊዝ ቅርስ ተቋማት ጥያቄ አቅርባ ነበር።
መቅደላ 1868

የፎቶው ባለመብት, V&A Museum
- በ19ኛው ክፍለ ዘመን ቴዎድሮስ ከእንግሊዝ ጋር ግንኙነት በመፍጠር አቢሲኒያን ለማዘመን ወሰኑ
- ነገር ግን የወታደራዊ ድጋፍ ጥያቄያቸው በእንግሊዝ ችላ በመባሉ የአገራቱ ግንኙነት ሻከረ።
- ለዚህ በምላሹም ቴዎድሮስ የእንግሊዝ ቆንስላና ሌሎች የውጭ አገር ዜጎችን አሰሩ።
- ይህን ተከትሎ እንግሊዝ ወደ መቅደላው የንጉሡ ቤተ መንግሥት ጦሯን ላከች።
- በእንግሊዞች እጅ አልወድቅም በማለት አጼ ቴዎድሮስ ራሳቸውን አጠፉ።
- የእንግሊዝ ጦርም ውድ ብራናዎችን፣ አክሊሎች፣ መስቀል፣ የወርቅ ዋንጫዎችን፣ የንጉሣዊያንና የቤተ ክርስትያን ቁሳቁሶችን ጋሻና የመሳሰሉትን ዘርፈው ወሰዱ።
- በጊዜው የንጉሡ የሰባት ዓመት ልጅም ወደ እንግሊዝ ተወስዶ በራግቢ ትምህርት ቤት እንዲማር ተደርጓል።

የፎቶው ባለመብት, V&A Museum
- ልጃቸው በ18 ዓመቱ በሳንባ በሽታ ሲሞት በዊንድሶር ቤተመንግሥት ተቀበረ።
- የእንግሊዙ ቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም የወርቅ አክሊልና ዋንጫ አስቀምጧል።
- ከመቅደላ የተዘረፉት ሌሎቹ ቅርሶች ከግለሰቦች ለሙዚየሙ በስጦታ የተበረከቱ ናቸው።












