ሶሪያዊው ስደተኛ በሶሪያ ጦርነት የግድያ ቪዲዮ ላይ 'በመታየቱ' በኔዘርላንድስ ለፍርድ ቀረበ

የሶሪያ ደጋፊ ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

በኔዘርላንድስ አንድ ስደተኛ በሶሪያ ጦርነት ወቅት ያልታጠቀ ግለብ ግድያ ላይ ተሳትፈሃል በሚል በጦር ወንጀል ክስ ተጠያቂ ሆኖ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

የ49 አመቱ አህመድ አል ኬ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ኔዘርላንድስ የመጣው በአውሮፓውያኑ 2014 ነው።

ግለሰቡ ያልታጠቀ የሶሪያ ወታደር ሲገደል የሚያሳይ ቪዲዮ ላይ መታየቱን ተከትሎ ከሁለት አመታት በፊት በቁጥጥር ስር የዋለው።

ግለሰቡ በወታደሩ ግድያ ወቅት መኖሩን ቢያምንም ጠበቆቹ እንደሚሉት በቦታው ላይ የተገኘው በእስር ቤት የነበሩ ወንድሞቹን ከምርኮኛው ጋር እንዲለዋወጡ በሚል አላማ ነበር በማለት ተከራክረዋል።

የተገደለው ግለሰብ የሶሪያ አየር ኃይል ኮሎኔልና የአልኑስራ ግንባር የጂሃዲስት መሪ አቡ ኩደር ነው።

አህመድ በአቡ ኩደር ግድያ ላይ አልተሳተፍኩም በማለት ክዷል።

ሶሪያዊው ስደተኛ ለፍርድ ሲቆም በኔዘርላንድስ የመጀመሪያ ቢሆንም በጀርመንና በስዊድን ግን ከዚህ ቀደምም ስደተኞች ለፍርድ ቆመዋል።

ቪዲዮው ምንን ያሳያል?

በአውሮፓውያኑ 2012 ነው የተቀረፀው የተባለው ቪዲዮ በቁጥጥር ስር የዋለ የሶሪያ አየር ኃይል ኮሎኔል በኤፍራጥስ ወንዝ ዳርቻ ሲወሰድና በዚያም በሽጉጥ ሲገደል ያሳያል።

መጀመሪያ በተገኘው ቪዲዮ ላይ ከሟቹ ኮሎኔል በስተቀር ሌላ ሰው የማይታይ ቢሆንም ከጀርመን መርማሪዎች በተገኘ ሁለተኛ ቪዲዮ ላይ የአሁኑ ተከሳሽ እንደሚታይ አቃቤ ህግ ተናግሯል።

ከዚያ በኋላ በነበረ ክትትልና ምርምር ተከሳሹ በኮሎኔሉ ግድያ ቪዲዮ ላይ ድምፁ እንደሚሰማ አምኗል።

አህመድ አኬ በጦር ወንጀልና በሽብር መከሰሱንም የደች የመንግሥት ሚዲያ ኤን ኦ ኡስ ዘግቧል።

በሶሪያ የሚገኝ አንድ የአይን እማኝም ስለሆነው ነገር ምስክርነቱን በዋትስ አፕ ለመርማሪዎች ተናግሯል።

ተከሳሹ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ለፍርድ ቤቱ እንደተናገረው በአውሮፓውያኑ 2013 ወደ ቱርክ እንደተሰደደና በግሪክም አቆራርጦ በዚህ አመት ሚያዝያ ወደ ኔዘርላንድስ እንደገባ ነው።

በኋላም ሚስቱና ሰባት ልጆቹ የመጡ ሲሆን ተከሳሹ በአካባቢው በሚገኝ የእግር ኳስ ክለብ በቁጥጥር ስር እስከዋለበት ወቅት ድረስ በበጎ ፈቃደኝነት ይሰራ እንደነበር የደች ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ጊዜያዊ ጥገኝነትም ተሰጥቶት ነበር።