እናቱን ገድሎ የበላው ስፔናዊ የ15 አመት እስር ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, Spanish Police
እናቱን ገድሎ የበላው ስፔናዊ የ15 አመት እስር ተፈረደበት።
የ28 አመቱ ሳንቼዝ ጎሜዝ በቁጥጥር ስር የዋለው ከሁለት አመት በፊት ሲሆን ፖሊስ የእናቱን የተወሰነ አካል ክፍሏን በቤቱ ውስጥም እንዳገኘም ተገልጿል።
ተገኘ የተባለውም የሰውነት አካልም በፕላስቲክ የዕቃ መያዣ ውስጥ ነው።
ተከሳሹ እናቱን መቆራረጡንና መብላቱን እንደማያስታውሰው ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
በግድያውም ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ የአዕምሮ መታወክ እንደገጠመው ለችሎቱ ቢያስረዳም ፍርድ ቤቱ መከራከሪያውን አልተቀበለውም።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ግለሰቡ እናቱን በመግደሉ 15 አመት የፈረደበት ሲሆን አስከሬኗንም ቆራርጦ በመብላቱ ተጨማሪ አምስት ወራት እስር በይኖበታል።
ከዚህም በተጨማሪ ለወንድሙ ካሳ እንዲሆን በሚል 73 ሺህ ዶላር ቅጣት እንዲከፍል ተጥሎበታል።
በስልሳዎቹ እድሜ ላይ የሚገኙት እናት ማሪያ ሶሌዳድ ጎሜዝ ይሰኛሉ።
ከሁለት አመታት በፊት ጓደኛቸው የደህንነታቸው ሁኔታ ስጋት ገብቶኛል ብለው በመናገራቸው ፖሊስ ወደቤታቸው ያመራ ሲሆን ቤታቸውንም ሲፈትሽ ነው የተቆራረጠ አካላቸውን ያገኘው።
በፍርድ ሂደቱም ላይ በእናትና ልጅ በተነሳ አለመግባባት ልጃቸው እንዳነቃቸውና እንደገደላቸው ተገልጿል።
በመቀጠልም ሰውነታቸውን እየቆራረጠ ለሁለት ሳምንት ያህል የበላ ሲሆን የተወሰነውንም ለውሻው ሰጥቷል ተብሏል።
ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በእናቱ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ያደርስ እንደነበርና እናቱ ጋር እንዳይደርስም ፖሊስ እግድ ጥሎበት እንደነበር የስፔን ሚዲያዎች ዘግበዋል።












