ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በየመን የጀልባ መስጠም አደጋ በርካታ ስደተኞች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተነገረ
በየመን ጠረፍ አቅራቢያ አንድ ጀልባ መገልበጧን ተከትሎ በደርዘን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች ህይወታቸው ሳያልፍ አይቀርም ተብሎ ተሰግቷል፡፡
በየመን ላህጅ ግዛት የሚገኙ ዓሳ አጥማጆች ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደገለጹት በራስ አል-አራ አቅራቢያ ከሚገገኘው ውሃ 25 አስከሬኖችን ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
አንድ የክልሉ ባለስልጣን እንደተናገሩት ከ 160 እስከ 200 የሚደርሱ ሰዎችን የያዘ ጀልባ ከሁለት ቀናት በፊት በአካባቢው ተገልብጧል፡፡
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን የያዘ መርከብ መስጠሙን የሚያረጋግጡ ዘገባዎችን እያጣራሁ ነው ብሏል፡፡
"የአይኦኤም አባላት በአካባቢው በመኖራቸው የተረፉ ሰዎችን ፍላጎት ለማገዝ ዝግጁ ናቸው፡፡" ሲል በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።
አደን አል-ጋድ የተባለ አንድ የየመን የዜና አውታር በበኩሉ እስከ 150 የሚደርሱ ስደተኞች መስጠማቸውን ከምንጮቹ ማግኘቱን ጠቁሞ አራት የመናውያን እንደሚገኙበትም አስታውቋል።
ራስ አል-አራ የመን እና ጅቡቲን የሚለይ እና የቀይ ባህርን ከባህረ ሰላጤው ጋር የሚያገናኝ 20 ኪ.ሜ ስፋት ያለው ነው። ከባብ አል-ማንዳብ በስተምሥራቅ ያለው አካባቢ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የሚጠቀሙበት የባህር ዳርቻ ነው፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከአፍሪካ ቀንድ በተለይም ከኢትዮጵያና ሶማሊያ የመጡ ስደተኞች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት መስመሩን አቋርጠው ወደ የመን ይሻገራሉ፡፡
ብዙዎቹ የህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎቹ ጀልባዎች ከመጠን በላይ የተጨናነቁ እና ለውሃው ተስማሚ ያልሆኑ በመሆናቸው ጉዞው በአደጋ የተሞላ ነው፡፡
በሚያዝያ ወር በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች የምትተዳደር ጀልባ ከየመን ወደ ጅቡቲ በመጓዝ ላይ ሳለች ተገልብጣ ቢያንስ 44 ስደተኞች ሞተዋል፡፡
ስድሰተኛ ዓመት ባስቆጠረ የእርስ በእርስ ጦርነት የምትታመሰው የመን የገቡ ብዙ ስደተኞች ቤተሰቦቻቸው እስኪከፍሉ ድረስ በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ ለቀናት ወይም ለወራት ተይዘው ይቆያሉ፡፡
አይኦኤም እንዳለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ የመን የሚደርሱ የስደተኞች ቁጥር ዝቅ ብሏል። በዚህ ዓመት 5100 ስደተኞቹ ሲገቡ እአአ በ2020 ቁጥሩ 35,000 ሲሆን በ 2019 ደግሞ 127,000 ደርሷል፡፡
የሳዑዲ አረቢያ ድንበር በመዘጋቱ እና የሥራ እድል አነስተኛ በመሆኑ ከ 32 ሺህ በላይ ስደተኞች በሀገሪቱ መፈናፈኛ አጥተው ተቀምጠዋል። ብዙዎች ምግብ፣ መጠለያ፣ ህክምና እና ደህንነት በማያገኙበት አደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ ይኖራሉ፡፡
ግጭቱ እአአ በ2015 ሲባባስ አማጽያኑ ሁቲዎች ሰፊውን የሀገሪቱን ክፍሎች ተቆጣጥረው የነበረ ሲሆን በሳዑዲ-የሚመራው የአረብ መንግስታት ጥምረት ደግሞ ፕሬዚዳንት አብድራቡህ መንሱር ሀዲን አገዛዝ ለማስመለስ ወታደራዊ ዘመቻ ጀመረ፡፡
በግጭቱ ከ 110,000 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል። የተባበሩት መንግስታት በዓለም ላይ እጅግ የከፋ የሰብአዊ ቀውስ ነው ሲል በሚገልጸፈው ክስተት 12 ሚሊዮን ሰዎች በምግብ እርዳታ የሚተዳደሩ ሲሆን ከአምስት አመት በታች ከሚሆኑት ህጻናት ግማሽ የሚሆኑት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል ተብሏል፡፡