ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኔቶ ከቻይና ተደቅኗል ስላለው ወታደራዊ ስጋት አስጠነቀቀ
በብራሰልስ የተገናኙት የየሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መሪዎች በቻይና ተደቅኗል ስላሉት ወታደራዊ ስጋት ያስጠነቀቁ ሲሆን "ስልታዊ እንቅፋት" ሲሉ የአገሪቷን ባህሪይ ገልጸውታል።
ቻይና የኒኩለር የጦር መሳሪያዋን በፍጥነት እያሰፋች መሆኗን ጠቅሰው የወታደራዊ አቅሟን በማዘመን ረገድ ግልፅ ነበረች ብሎም ከሩሲያ ጋርም በወታደራዊ ትብብር እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።
የኔቶ ዋና ሃላፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ ቻይና በወታደራዊ እና በቴክኖሎጂ ረገድ ወደ ኔቶ "እየቀረበች" እንደሆነ አስጠንቅቀዋል ። ነገር ግን ጥምረቱ ከቻይና ጋር አዲስ የቀዝቃዛ ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማይፈልግ አጥብቀው ተናግረዋል ።
ኔቶ በ 30 የአውሮፓ አገራት እና በሰሜን አሜሪካ ሀገሮች መካከል የተመሰተ ጠንካራ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ጥምረት ነው ። የተቋቋመውም ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ሲሆን በተለይም ለኮሚኒስት ስርአት መስፋፋት ስጋት ምላሽ ለመስጠት ያሰበ ነበር።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሪዎች በዓላማው ብሎም የገንዘብ መዋጮን በተመለከተ ያለመግባባት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ጥምረቱ ውጥረት ውስጥ ከርሟል ።
በዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ወቅት ሀገራቸው ለህብረቱ በምታዋጣው የገንዘብ መጠን ላይ ቅሬታ ሲያሰሙ የቆዩ ሲሆን አሜሪካ የአውሮፓ አገራትን ለመከላከል ያላትን ቀርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነበር።
የእሳቸው ተተኪ ጆ ባይደን ስልጣኑን ከያዙ ወዲህ የመጀመሪያ የኔቶ ስብሰባ ሲሆን አዲሱ ፕሬዝዳንት ለ 72 ዓመቱ ህብረት የአሜሪካን ድጋፍ በድጋሚ ለማሳየት ሞክረዋል ።
ባይደን ኔቶ "ለአሜሪካ ፍላጎቶች" ወሳኝ ጠቀሜታ እንዳለው እና አባላት የጥመረቱን የመመሰረቻ ውል አንቀጽ 5 ን በመተግበር እርስ በእርስ ከጥቃት ለመከላከል የተቀመጠውን "የተቀደሰ ግዴታ" እንዲተገብሩ ጠይቀዋል ።
መጪው ረቡዕ ከሩሲያው መሪ ከቭላድሚር ፑቲል ጋር በጄኔቫ ስለሚያካሂዱት ስብሰባ ሲጠየቁ ‹‹ጠንካራ ተፎካካሪ›› ሲሉ ፑቲንን ገልፀዋቸዋል።