ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምርመራ ከተከፈተባቸው የቀድሞ ኃላፊ ጋር ጎልፍ የተጫወቱት ካናዳዊ ጄኔራል ከስራ ለቀቁ
በካናዳ ጦር ምክትል አዛዡ ሰው ከአገሪቱ ከቀድሞ የመከላከያ አዛዥ ጋር ጎልፍ በመጫወታቸው ከስልጣን ለቀቁ።
የቀድሞው አዛዥ በጦሩ ውስጥ ያልተገባ ወሲባዊ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል።
ስራቸውን የለቀቁት ጄኔራል ማይክ ሮሉ እንዳሉት የቀድሞው የመከላከያ አዛዥ ጄኔራል ጆናታን ቫንስንን ለጎልፍ ጨዋታ የጋበዙዋቸው የጤንነታቸውን ሁኔታ ለማወቅ ነበር።
ጄኔራል ማይክ በነበራቸው ስልጣን የቀድሞ የመከላከያ አዛዡን ጨምሮ ሁሉንም ወታደራዊ ምርመራዎች በበላይነት ያያሉ።
ጄኔራሉ ግን ስለ ምርመራው ዝርዝር ምንም አልጠቀስንም ብለዋል።
ነገር ግን ያልተገባ ወሲባዊ ግንኙነት ምርመራ ከተከፈተባቸው ሰው ጋር ጎልፍ ሲጫወቱ መታየታቸው ሁኔታዎችን እንዳጋጋለውና ህዝቡ በጦሩ ላይ ያለው እምነት በበለጠ እንዲሸረሸር እንዳደረገው ነው።
በጥር ወር በጡረታ የተሰናበቱት ጄኔራል ጆናታን የተከፈተባቸውን ምርመራ በሙሉ አይቀበሉትም።
ሁለቱ ጄኔራሎች ጎልፍ የመጫወታቸው ዜና የወጣው በአገሪቱ ሚዲያዎች ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይልና ግሎባል ኒውስ ላይ በባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነው።
ጄኔራሉም በኦታዋ ምርመራ ከተከፈተባቸው ጄኔራልና ከካናዳ አየር ኃይል ኃላፊ ክሬይግ ቤይንስ ጋር ጎልፍ መጫወታቸውን አምነው ደብዳቤ ፅፈዋል።
ጄኔራሉ የአየር ኃይል ኃላፊው ለዚህም ተጠያቂ መሆን እንደሌለባቸውና ሙሉ በሙሉም የሳቸው ኃላፊነት እንደሆነ አሳውቀዋል "እኔ ባልኖር ኖሮ ኃላፊው አይመጡም" ብለዋል።
ነገር ግን የአየር ኃይል ኃላፊው በበኩላቸው እሁድ እለት ለብቻቸው በሰጡት መግለጫ ይቅርታ ጠይቀዋል።
ጄኔራል ጆናታል በጦሩ ወስጥ ከነበሩት ኬሊ ብሬናንና ሌላ ሴት ጋር የነበራቸው ግንኙነት ወታደራዊ ህጎችን ይጥሳል በሚል ነው ምርመራ የተከፈተባቸው።
ከዚህም በተጨማሪ ጄኔራሉ በጦሩ ውስጥ ላለች አንዲት ሴት ወሲባዊ መልዕክት ያለው ኢሜይል ፅፈዋል ተብሏል።
በቅርብ አመታት የካናዳ ጦር በወሲባዊ ጥቃቶች ክስ ምክንያት ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብቷል።