ሶኒ በሺዎች የሚቆጠሩ አርቲስቶችን እዳ ሰረዘ

ሶኒ በሺዎች የሚቆጠሩ አርቲስቶችን እዳ ሰረዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሶኒ ሚውዚክ ከአውሮፓውያኑ 2000 በፊት ከድርጅቱ ጋር ውል የተፈራረሙ በሺዎች የሚቆጠሩ አርቲስቶችን እዳ መሰረዙን አስታውቋል።

እዳቸውን መክፈል አቅቷቸው የነበሩ በርካታ ሙዚቀኞች እንደ ስፖቲፋይ እና አማዞን ሚውዚክ የመሳሰሉ መተግበሪያዎች ላይ ሙዚቃዎቻቸውን ሲሸጡ ገንዘቡን በቀጥታ ያገኛሉ ማለት ነው።

አብዛኛዎቹ አርቲስቶች ለዓመታት በነዚህ መተግበሪያዎች በኩል የሚያገኙትን ገቢ እዳቸውን ነበር የሚከፍሉበት።

ከዚህ በኋላ ግን ጥቂት የማይባሉ አርቲስቶች በዓመት በሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ያገኛሉ ማለት ነው።

በሙዚቃው ኢንዱስትሪ አዳዲስ ዘፋኞች እንደ ሶኒ ካሉ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ሲያደርጉ፤ ሠርተው የሚከፍሉት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል። ገንዘቡም ቀላል እንዳልሆነ በርካቶች ይናገራሉ።

ገንዘቡን ሙዚቃዎቻቸውን ለመቅረጽ፣ ለስቱዲዮ፣ ለቪዲዮ፣ የሲዲ ስርጭት እንዲሁም ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን ይጠቀሙበታል።

ሙዚቃዎቹ ተወዳጅነት አግኝተው አድማጭ በደንብ መግዛት ሲጀምር ደግሞ ከሚያገኙት ገንዘብ ለድርጅቱ መክፈል ይጀምራሉ።

ነገር ግን በርካታ አርቲስቶች እዳቸውን ለመክፈል የሚያስችል ሽያጭ ስለማያደርጉ እራሳቸውን እዳ ውስጥ ተዘፍቀው ያገኛሉ። ይህን ተከትሎም በማንኛውም መንገድ በሙዚቃ ሥራቸው የሚያገኙትን ገንዘብ ሰብስበው እንደ ሶኒ ላሉ ድርጅቶች መክፈል ግዴታቸው ነው።

በ1990ዎቹ ታዋቂ የነበሩት ቲኤልሲ፤ ከሶኒ ጋር በወቅቱ ስምምነት አድርገው የነበረ ሲሆን፤ ባጋጠማቸው ኪሳራ እዳቸውን መክፈል ሳይችሉ ቀርተዋል። በዚህም ምክንያት በይፋ ኪሳራ ውስጥ መግባታቸውን አስታውቀው ነበር።

የአርኤንድቢ ኮከቦቹ ለበርካታ ዓመታት አልበማቸው በብዛት ሲሸጥ የነበረ ቢሆንም፤ መጨረሻ ላይ ግን 3.5 ሚሊየን ዶላር እዳ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ሶኒ ሚውዚክ ምን አለ?

የሶኒ ያልተጠበቀ ውሳኔ ትናንት አርብ ሲሆን ይፋ የተደረገው ቢቢሲም የዚህን መረጃ ግልባጭ ማግኘት ችሏል።

"አሁን ያሉ ኮንትራቶችን አይደለም እያስተካከልን ያለነው። ነገር ግን ከዚህ በኋላ ሙዚቃቸውን ሠርተው ለአድማጭ ማድረስ የሚፈልጉና ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት የሚፈልጉትን አርቲስቶች ለማበረታታት ነው" ብሏል ድርጅቱ።

በሌላ አገላለጽ እዳው ሙሉ በሙሉ ተሰርዟል ማለት አይደለም። ነገር ግን ሶኒ እዳውን ችላ ይለውና እስከ ጥር 2021 ድረስ ጉዳት ለደረሰባቸው የመብት ክፍያ እና የሚያስፈልጋቸውን ለማካተት ነው።

የሙዚቃ ዘርፍ የሕግ ባለሙያ የሆኑት አውሬሊያ በትለር እንደሚሉት፤ ይህ አዲስ አሠራር ከዚህ በፊት በተለያዩ የሙዚቃ ማሰራጫ መንገዶች በኩል አርቲስቶቹ ሊያገኙት ይገባ የነበረውን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው።

"ይህ ተግባራዊ የሚሆነው ከሶኒ ጋር ሙዚቃዎች በሲዲ እና ካሴት በሚሸጡበት ዘመን ስምምነት ለተፈራረሙ አርቲስቶች ብቻ ነው" ብለዋል።

"ከ2000 በፊት የተደረጉ ስምምነቶች ላይ አርቲስቶቹ በዘመናዊው ዓለም ሙዚቃ በበይነ መረብ ብቻ ይቸበቸባል ብለው አላሰቡም ነበር። ለዚህም ነው ስምምነቱን ያደረጉት። በዚህ ምክንያት እነዚህ አርቲስቶች ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሳያገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ሲከፍሉ ነው የቆዩት።"

ይህ የሶኒ ውሳኔ የመጣው በሙዚቃው ዘርፍ ያለው የገንዘብ ክፍፍል፣ ዘመናዊ የሙዚቃ ማሰራጫ መንገዶችን በተመለከተና ሌሎች ጉዳዮች ላይ መሻሻያዎች መደረግ አለባችው የሚሉ ሰዎች በበረከቱበት ወቅት ነው።

የጎሜዝ ሚውዚሺያን አባል የሆነው ቶም ግሬይ፤ መሰል ተግባራት እንዲጀመሩና አርቲስቶች ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም በሙሉ እንዲያገኙ ሲሠራና እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ነበር። የሶኒንም ውሳኔ በጣም አስደሳች ብሎታል።

"እነዚህ ትልልቅ ድርጅቶች ሥነ ምግባር በተሞላበትና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲሠሩ ለማድረግ ለበርካታ ዓመታት ሲሠራ ለነበረ ሰው ይህ ዜና በጣም አስደሳችና እንደ ትልቅ ድል የሚታይ ነው" ብሏል ለቢቢሲ ሲናገር።

ሌሎች ድርጅቶች የሶኒን ፈለግ ይከተሉ ይሆን?

መሰል እርምጃ በመውሰድ ሶኒ የመጀመሪያው ድርጅት አይደለም።

ኢንዲ ሌብል ቤጋርስ ግሩፕ የተባለው ድርጅት ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ የአርቲስቶችን ያልተከፈለ እዳ ሰርዞ ነበር። ነገር ግን እንዲህ አይነት ውሳኔ ያስተላለፈ ትልቅ ድርጅት ከሶኒ በቀር የለም።

የሶኒ ቀጥተኛ ተፎካካሪ የሆኑት ዩኒቨርሳል እና ዋርነር ሚውዚክ ምናልባት ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ሊያስቡ ይችላሉ።

ነገር ግን ቶም ግራይስ እንደሚለው፤ ድርጅቶቹ ከዚህም አልፈው ለአርቲስቶቹ ለሙዚቃ መብታቸው የሚከፈው ዝቅተኛ ገንዘብ ከፍ መደረግ አለበት ብሎ ያምናል።

"የአንድ አርቲስት ክፍያ ከሚገኘው ገቢ 5 በመቶ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፍ ማግኘት አይችሉም። ክፍያው ከፍ ማለትም አለበት" ብሏል።