ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ የቀረጸችው ወጣት ሽልማት ተበረከተላት
ጆርጅ ፍሎይድ በነጭ የፖሊስ መኮንን ሲገደል የሚያሳየውን ቪዲዮ የቀረጸችው ወጣት ከፑልትዘር ቦርድ ልዩ የጋዜጠኝነት ሽልማት ተሰጣት፡፡
የ18 ዓመቷ ዳርኔላ ፍሬዜርን ድፍረት በመጥቅስ ሽልማት እንደተበረከተላት የፑልትዘር ኮሚቴ ገልጿል፡፡
ቪዲዮው በዓለም ዙሪያ የዘር መድልዎን የሚቃወሙ ሰልፎችን ያነሳሳ ሲሆን የፖሊስ መኮንኑ ዴሪክ ቻውቪንን የፍርድ ሂደት ላይ እንደ ማስረጃ አገልግሏል፡፡
ፑልትዘር አሜሪካ ውስጥ በጣም የታወቀ የጋዜጠኝነት ሽልማት ነው፡፡
ኮሚቴው "የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ በድፍረት በመቅረጽ በዓለም ዙሪያ በፖሊስ ጭካኔ ላይ የተቃውሞ ሰልፎችን በማነሳሳት፤ የማኅበረሰብ ጋዜጠኞች የእውነትና የፍትህ ጥያቄ ላይ ያላቸውን ወሳኝ ሚና ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ቪዲዮ ነው" ብሏል፡፡
ፍሬዜር ባለፈው ዓመት ግንቦት ከአጎቷ ልጅ ጋር በሚኒያፖሊስ በእግር ሲጓዙ ሳሉ ፍሎይድ በቁጥጥር ሥር ሲውል ተመለከቱ፡፡
"አንድ ሰው በፍርሀት ለነፍሱ ሲለምን" አይታ ድርጊቱን በስልክ መቅረጽ እንደጀመረች በዚህ ዓመት መጀመሪያ ለፍርድ ቤት ተናግራለች፡፡
ፍሬዜር ፍሎይድ "መተንፈስ አልችልም" እያለ በጣም ፈርቶ እናቱን እየጠራ ነበር ስትል አስታውሳለች፡፡
ቪዲዮው በዓለም ዙሪያ የታየ ሲሆን በአሜሪካ ከፍተኛ ተቃውሞዎች እና ቁጣን አስነስቷል፡፡ ለብዙዎች ፍሎይድ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እያለ መሞቱ የፖሊስ ጭካኔ ምልክት ሲሆን፤ በዓለም ዙሪያ የዘር መድልዎን የሚቃወሙና ፍትሕ የሚጠይቁ ሰልፎችን ቀስቅሷል፡፡
ቀረጻው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በቻውቪን የፍርድ ሂደት ላይ እንደ ማስረጃ ቀርቧል። በኋላም ፖሊሱ በሦስት ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
የፍሎይድን ግድያ ማየቷ ሕይወቷን እንደለወጠው ፍሬዜር ለፍርድ ቤቱ ተናግራች፡፡
"ጆርጅ ፍሎይድን ስመለከት አባቴን እመለከታለሁ፣ ወንድሜን፣ የአጎቶቼን ልጆች፣ አጎቶቼን እመለከታለሁ። ምክንያቱም ሁሉም ጥቁር ናቸው፡፡ በአንዳቸው ላይ ተፈጽሞ ቢሆንስ እላለሁ" ስትል እያነባች ተናግራለች።