የኮንጎ ተወላጁ የስቱትጋርት አጥቂ በሐሰተኛ ስም ሲጫወት ነበር ተባለ

ሲላስ ካቶምፓ ምቩምፓ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የዓመቱ ምርጥ አዲስ ተጫዋች በሚል ሽልማት የተቀበለውና በጀርመን ቡንደስሊጋ የሚሳተፈው የስቱትጋርት እግር ኳስ ክለብ ተጨዋች የሆነው ሲላስ ዋማንጊቱኪያስ በሐሰት መዝገብ ሲንቀሳቀስ ነበር ተባለ።

የዴሞክራቲክ ኮንጎ ተወላጁ ሲላስ ዋማንጊቱኪያስ ትክክለኛ ስሙ ሲላስ ካቶምፓ ምቩምፓ ሲሆን የተወለደው ደግሞ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት ወር 1998 ነበር።

ይህ መረጃ ደግሞ እሱ ከተናገረውና መረጃ ካቀረበበት ጋር ሲነጻጸር በአንድ ዓመት እድሜውን ከፍ ያደርገዋል።

ተጫዋቹ እንደሚለው ከሆነ እድሜውን ቀንሶ እንዲናገር ከፍተኛ ጫና ያደረሰበት የቀድሞ ወኪሉ ነበር። በዚህም ምክንያት 'በከፍተኛ ፍርሀት' ውስጥ እንደቆየ ተናግሯል።

ስቱትጋርት እግር ኳስ ክለብ ደግሞ ጉዳዩን ካረጋገጠ በኋላ ከቡንደስሊጋ እና የጀርማን እግር ኳስ ማሕበር ጋር ንግግር ማድረግ ጀምሯል።

ክለቡም ከ22 ዓመቱ ወጣት ተጨዋች እና አዲሱ ወኪሉ ጋር ንግግር እያደረገ እንደሆነና ጉዳዩን በጥልቀት እየመረመረው እንደሆነ አስታውቋል።

ክለቡ ጨምሮም ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ይፋዊ መረጃዎችን ከጥቂት ቀናት በፊት ማግኘቱን ገልጿል።

ተጨዋቹ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በጀርመን ቡንደስሊጋ 13 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ተጨዋቹ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በጀርመን ቡንደስሊጋ 13 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል

ሲላስ ዋማንጊቱኪያስ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በጀርመን ቡንደስሊጋ 13 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ክለቡ ስቱትጋርትም ዘጠነኛ ሆኖ ማጠናቀቅ እንዲችል ረድቷል።

በአውሮፓውያኑ 2017 ለቤልጂየሙ አንደርሌክትም ተጫውቶ የነበረ ሲሆን በቀድሞ ወኪሉ ገፋፊነት ደግሞ በፈረንሳይ ሁለተኛ ሊግ ወደሚጫወተው ፓሪስ እግር ኳስ ክለብ ተዘዋውሯል።

2019 ላይ ደግሞ ስቱትጋርትን በመቀላቀል ቡድኑ ወደ ጀርመን ቡንደስሊጋ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

"ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኮንጎ ለሚገኙት ቤተሰቦቼ ጭምር እሰጋ ነበር" ብሏል ተጨዋቹ።

"የግል ታሪኬን ለህዝብ ይፋ ለማድረግ መወሰን በጣም ከባድ ነገር ነበር። ነገር ግን ስቱትጋርት እግር ኳስ ክለብ እንደ ቤቴ የምቆጥረውና የማምነው ክለብ በመሆኑ ድፍረቱን አግኝቻለሁ" ብሏል።