በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሁለት ወራት ውስጥ ለለቅሶ እና ለሠርግ በተተኮሰ ጥይት 12 ሰዎች ተገድለዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዘላለም አበበ ቀኑን በውል በማያስታውሰው ቅዳሜ ዕለት፤ በሙያው መምህር የሆነው ወንድሙ ወደሚኖርበት ፍኖተ ሠላም ከተማ ተጉዞ ሲጨዋወቱ ውለው አድረዋል።
በማግሥቱ ሌሎች ቤተሰቦች ሠርግ አጅቧቸው ወደ መርዓዊ እንዲሄዱ እንግዳውን ይጠይቁታል። ወንድም ብዙም ጤና እተሰማው ስላልነበረ መሄድ ባይፈልግም ተደጋጋሚ ጥያቄ ስለቀረበለት ጥያቄውን ተቀበለ።
በማግስቱ እሑድ ጠዋት ከሙሽራው ጋር የሚስት ቤተሰቦች ወደሚገኙበት መርዓዊ ጉዟቸውን አደረጉ።
በዚያው ዕለት ከቀኑ 9፡00 አካባቢ ግን ያልተጠበቀው ክስተት ተፈጠረ።
የዘላለም ወንድም በሠርግ ሥነ ሥርዓቱ መካከል በተተኮሰ ጥይት ተመቶ መሞቱን እንደሰማ እና በሕይወት የሸኘው ወንድሙን ከሰዓታት በኋላ አስከሬኑን ለመቀበል መገደዱን ይናገራል።
ለቤተሰባቸው ሟች ታላቅ መሆኑን የሚናገረው ዘላለም፤ አባታቸው ገና እርሱ የስድስት ዓመት ታዳጊ እያለ ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ እንደ ትልቅ ወንድም ኃላፊነት ወስዶ፣ አስተምሮ፣ ለቁም ነገር ያደረሰው ወንድሙ እንደሆነ በጥልቅ ሐዘን ገልጿል።
ሟች ወንድሙ በፍኖተ ሰላም ከተማ መምህር እና የአንድ ልጅ አባት እንደነበር የሚናገረው ዘላለም፤ ያስተማረው ወንድሙ ቤተሰቡን ማገዝ ሲጀምር ባልተጠበቀ አደጋ ሕይወቱን አጥቶ ቤተሰቡ ዳግም ወደሌላ ችግር መግባቱን ገልጿል።
እስካሁን የወንድሙ ገዳይ ማን እንደሆነ አለመታወቁንና በወቅቱ በርካታ ተኩስ ይሰማ ስለነበር ከማን በተተኮሰ ጥይት ተመትቶ እንደሞተ አለመታወቁንም ተናግሯል።

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ለደስታ ማድመቂያ ወይም በሐዘን ወቅት በሚተኮስ ጥይት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
ችግሩ በብዛት ከሚስተዋልባቸው የክልሉ ዞኖች መካከል የምሥራቅ ጎጃም ዞን አንዱ ነው። በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ችግሩ እንደሚያጋጥም የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮምዩኒኬሽንና ሚዲያ ባለሙያ ዋና ሳጅን ስሜነህ በላቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ዋና ሳጅን ስሜነህ፤ በየጊዜው የጦር መሣሪያ አጠቃቀምን በተመለከተ እና በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ላይ የሚደረግ ተኩስን አላስፈላጊነት ሁሉንም የአካባቢውን የጸጥታ መዋቅር በመጠቀም ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ነገር ግን በአካባቢው በለቅሶ እና በሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ወቅት በሚተኮስ ጥይት ተመተው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ ነው ብለዋል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት የግንቦት ወር ድረስ ከሚያዝያ ወር አንስቶ [ከፋሲካ በዓል ወዲህ] በምሥራቅ ጎጃም ዞን ብቻ ለሠርግ እና ለቅሶ ተብሎ በተተኮሱ ጥይቶች 18 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ከእነዚህ መካከል የ12 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን 6 የሚሆኑት ደግሞ በተለያየ ደረጃ የሚገለጽ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚተኮስ ጥይት ሳቢያ የሚደርስን ጉዳት ለማስቀረት "ለማኅበረሰቡ የጦር መሣሪያ አያያዝን እና ሕገ ወጥ ተኩስን በተመለከተ በተደጋጋሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ቢሠራም እምብዛም ለውጥ እንዳልመጣ" ዋና ሳጅን ስሜነህ አመልክተዋል።
ሁሉም የጸጥታ መዋቅር በተገኘው አጋጣሚ ሕገ ወጥ ተኩስን ለማስቀረት ጥረት እያደረገ ቢሆንም ነዋሪው ግን ሠርግ እና ለቅሶን በጥይት ማድመቅን እንደ ባህል በመውሰድ ከተግባሩ ሊቆጠብ አለመቻሉን አክለዋል።
ሁለት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከሞቱት 12 ሰዎች መካከል አንዱ የሚሊሻ አባል መሆናቸውን የተናገሩት ዋና ሳጅን ስሜነህ፤ የሚሊሻ አባሉ በአንድ ሠርግ ላይ ሕገ ወጥ ተኩስ ሲደረግ ያንን ለማስቆም "አትተኩሱም፣ እንተኩሳለን በሚል በተፈጠረ ግብግብ ሚሊሻው ተገድሏል" ብለዋል።
በተለይ በሠርግ ላይ በአብዛኛው የሚተኮሰው በስካር ስሜት ውስጥ በመሆን ስለሆነ በቸልተኝነት፣ በእንዝህላልነት እንዲሁም መሣሪያን መቆጣጠር ባለመቻል ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎች መሆናቸውን ዋና ሳጅኑ ተናግረዋል።
በአብዛኛው በጉዳቱ ሰለባ የሚሆኑት የሠርገኞቹ የቅርብ ቤተሰቦች እና አጃቢዎች እንደሚሆኑ ገልጸው፤ አልፎ አልፎም አደጋው ሙሽሮች ላይ የሚደርስበት አጋጣሚ መኖሩን አክለዋል።
በአደጋው የሰው ሕይወት ከመጥፋቱም በላይ የሟች ቤተሰቦች ሜዳ ላይ የሚበተኑበት፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን የሚያቋርጡበት፣ ሕጻናት እና አዛውንቶች ረዳት የሚያጡበት ሁኔታ እየተፈጠረ ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢው 'ደም ምለሳ' የሚባል ባህል በመኖሩ የሟች ቤተሰቦች የገዳይ ቤተሰቦችን በማሳደድ ለብቀላ መነሳሳታቸው ውስብስብ ማኅበራዊ ቀውስ እያስከተለ በመሆኑ፤ ይህንን ለማስቀረት መሥራት እንደሚገባም ዋና ሳጅን ስሜነህ አሳስበዋል።












