ምርጫ 2013፡ በኢትዮጵያ ከሚካሄደው ምርጫ አንጻር የሚያሳስቧት ነገሮች እንዳሉ አሜሪካ ገለጸች

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት
ታትሟል

አሜሪካ መጪው የኢትዮጵያ ምርጫ በሚካሄድበት ጊዜ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ በእጅጉ እንደሚያሳስባት ገለጸች።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች እስር፣ በነጻ ሚዲያ ላይ የሚደርስ ወከባ፣ የብሔር ግጭቶችና ሌሎችም በምርጫው ነጻ እና ፍትሃዊነት ላይ የተጋረጡ ፈተናዎች መሆናቸውን ጠቅሷል።

ጨምሮም ከፍተኛ ቁጥር ያለው መራጭ ሕዝብ "በደኅንነት ችግሮች ምክንያትና በመፈናቀላቸው ሳቢያ በምርጫው የማይሳተፉ መሆናቸው አሳሳቢ" መሆኑን አመልክቷል።

ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታስቦ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ስጋት ምክንያት ወደዚህ ዓመት የተሸጋገረው ብሔራዊ ምርጫ፤ ባለፈው ግንቦት ወር ማብቂያ ላይ ሊካሄድ የነበረ ሲሆን በመራጮች ምዝገባ መራዘምና በምርጫ ቁሳቁሶች አቅርቦት መዘግየት ሳቢያ በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ ይካሄዳል።

ከቀናት በፊት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው፤ ኢትዮጵያ በሁለት ዙር የተከፈለ ምርጫ ለማካሄድ የተዘጋጀች ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ከአንድ ሳምንት በኋላ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች ይካሄዳል።

ሁለተኛው ዙር በጸጥታ ችግርና የተለያዩ የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች በወቅቱ አለመድረስና በሌሎች ችግሮች ምክንያት በዓመቱ ማብቂያ ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም እንሚካሄድ ተገልጿል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በመግለጫው፤ ይህ ምርጫ መታየት ያለበት እንደ አንድ ተናጠል ሁነት ሳይሆን ውይይትን፣ ትብብርንና ማመቻመችን ያካተተ የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ አንድ አካል ተደርጎ መሆን አለበት ብሏል።

ጨምሮም ለዚህ ደግሞ "የአገሪቱን ዴሞክራሲና ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከር መንግሥትና ኢትዮጵያውያን ሁሉን አካታች፣ ድኅረ ምርጫ ፖለቲካዊ ውይይት" እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በመግለጫው፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን በግጭቶችና በከባድ የምግብ እጥረት ለሞትና ለስቃይ በተጋለጡበት ጊዜ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫው የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቋል።

የፖለቲካና የማሕበረሰብ መሪዎችም ግጭቶችን እንዲቃወሙ እንዲሁም ሌሎችን ለግጭት ከማነሳሳት በመቆጠብ፣ ቅሬታዎችን በድርድር፣ በውይይትና በሌሎች ከኃይል በራቁ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች መፍትሔ እንዲፈልጉ ጠይቋል።

ጨምሮም መንግሥት ነጻ ሚዲያንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ማኅበራትን እንዲደግፍና የዜጎችን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ መብቶችን እንዲያከብር እንዲሁም ኢንተርኔት ከመዝጋትና ኔትወርኮች ላይ እቀባ ከመጣል እንዲቆጠብ ጠይቋል።

በበርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ እየጠነከረ የመጣው ክልላዊና የብሔር ክፍፍል የአገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ ጥሏል ያለው መግለጫው፤ ከምርጫው በኋላ ያለው ጊዜ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እነዚህን መከፋፈሎች እንዲጋፈጡ ወሳኝ ነው ብሏል።

ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች እንድትወጣና ብሩህ ተስፋ ያለበትን መንገድ እንድትከተል ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ገልጾ፤ ኢትዮጵያን መልካም ተስፋ ያላት፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ከሚጥሩ ዜጎቿ ጎንም እንደሚቆም ገልጿል።

በስድስተኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ 47 ፓርቲዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ለክልልና ለአገራዊ ምክር ቤቶች የቀረቡት ዕጩዎች ቁጥርም 8209 መሆኑ ቀደም ብሎ መገለጹ ይታወሳል።

በምርጫ ድምጽ ለመስጠትም ከ37 ሚሊየን ሕዝብ በላይ መመዝገቡን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።