የባይደን አስተዳደር ዶ/ር ፋውቺ ስለቫይረሱ አመጣጥ የሚያውቁት የለም እያለ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የፕሬዝደንቱ ከፍተኛ የኮሮናቫይረስ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አንተኒ ፋውቺ በቅርቡ የኢሜይል ልውውጣቸው መለቀቁን ተከትሎ ዋይት ሃውስ እየተሟገተላቸው ነው።
ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ጄን ሳኪ፤ ዶ/ር ፋውቺ አሜሪካ ኮቪድ-19ን በምትዋጋበት ወቅት ትልቁን ሚና ተጫውተዋል ሲሉ ተደምጠዋል።
ዶ/ር ፋውቺ በበኩላቸው ቫይረሱ ከየት መጣ የሚለውን ሐሳብ የሚያሳየው ኤሜይላቸው ከአውድ ውጭ እንደተወሰደባቸው ለሲኤንኤን ተናግረዋል።
የኮቪድ-19 ቫይረስ ከቤተ ሙከራ እንደመጣ የሚጠቁም ማስረጃ ባይኖርም ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ግን ምንጬ እንዲጣራ አዘዋል።
ፕሬዝደንቱ አክለው 25 ሚሊዮን ክትባቶች ኮቫክስ ለተሰኘው ክትባት ለደሃ ሃገራት ለሚያድለው ማዕቀፍ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።
ፕሬስ ሴክረታሪዋ ሐሙስ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት "ፕሬዝደንቱና አስተዳደራቸው ዶ/ር ፋውቺ ወረርሽኙን በቁጥጥር ሥር በማዋል ረገድ ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ያምናሉ፤ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የሕዝቡ ድምፅ ሆነው ቆይተዋል" ብለዋል።
ዶ/ር ፋውቺ በኮሮናቫይረስ ወቅት የተፃፃፏቸው 3200 ገፅ ያላቸው የኢሜይል ልውውጦች በዚህ ሳምንት እንዲለቀቁ ተደርገዋል።
የጉምቱው ዶክተር ኢሜይል ልውውጥ ይፋ እንዲሆነ የሆነው መረጃ የማግኘት ነፃነትን ተገን አድርጎ ነው።
የአሜሪካ ጤና ተቋማት አባላት ዶ/ር ፋውቺ በጣም ጠንካራ ሕዝብ አገልጋይ መሆናቸውን ነው ኢሜይላቸው የሚያሳየው ይላሉ።
ነገር ግን ወግ አጥባቂዎች ዶክተሩ የቫይረሱ ምንጭ ከወደየት እንደሆነ እንዳይታወቅ ሸፋፍነዋል፤ በኮንግረስ ፊት ቀርበው ሊመሰክሩ ይገባል ይላሉ።
ሐሙስ ዕለት በሲኤንኤን የታዩት ዶ/ር ፋውቺ በኤሌክትሮኒክስ ልውውጡ ላይ ምንም የተለየ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
ብሔራዊው የጤና ተቋማት ኤጀንሲ ከ2014 እስከ 19 ባለው ጊዜ ኮቪድ-19 ለመጀመሪያ ጊዜ የታየባት ዉሃን ለሚገኝ ተቋም 600 ሺህ ዶላር እርዳታ ሰጥቷል።
እርዳታው የተላለፈበት መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ኃላፊ በፈረንጆቹ ጥር 2020 ለዶ/ር ፋውቺ በላኩት መልዕክት ላይ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ነው የወጣው የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ ውድቅ በማድረጋቸው አሞጋግሰዋቸው ነበር።
ዶ/ር ፋውቺ በበኩላቸው 'ለመልዕክቱ እጅግ አሰመግናለሁ' ሲሉ መልሰዋል።
ፋውቺ ለሲኤንኤን ሲናገሩ ከዚህ ልውውጥ በመነሳት እሳቸውና የዉሃን ቤተ ሙከራ ግንኙነት አላቸው ብሎ ማሰብ 'ስሜት የማይሰጥ' ነው ብለዋል።
"ቻይናዎች ሆን ብለው ራሳቸውንና ሌሎችንም ሊገድል የሚችል ቫይረስ ሠርተዋል የሚባለው ለእኔ ብዙም የሚያስኬድ ፅንሰ ሐሳብ አይደለም" ብለዋል ፋውቺ።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሆን ብሎ ዉሃን ከሚገኘው ቤተ ሙከራ እንዲሾልክ ተደርጓል የሚለው ያልተረጋገጠ ፅንሰ ሐሳብ በአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት አግኝቷል።
ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል የመጀመሪያው የኮቪድ-19 ሕመምተኛ ከመታወቁ በፊት ሶስት የዉሃን ተህዋሳት ምርምር ተቋም ሠራተኞች ታመው ሆስፒታል ገብተው ነበር ሲል ፅፏል።
ከመገናኛ ብዙሃኑ ዘገባ በኋላ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የስለላ ተቋማቸው በ90 ቀናት ውስጥ ቫይረሱ ከቤተ-ሙከራው ሆን ተብሎ ነው የተለቀቀው ወይስ አይደለም የሚለውን እንዲያጣራ አዘዋል።
ቫይረሱ ከቻይና እንዲያመልጥ ተደርጓል ብለው የሚያምኑት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዶ/ር ፋውቺ ብዙ የሚመልሷቸው ጥያቄያዎች አሉ ሲሉ ተደምጠዋል።
"ቻይና በዓለምና በአሜሪካ ላይ ላደረሰችው ጥፋት 10 ትሪሊዮን ዶላር ልትከፍል ይገባል" ብለዋል ትራምፕ በለቀቁት መግለጫ።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቫይረሱ ከውሃን ቤተ ሙከራ ነው ያመለጠው የሚለውን ሐሳብ 'ፈፅሞ የማይሆን' ሲሉ አጣጥለውታል።
ኮቪድ-19 ዓለምን ከወረረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን 172 ሚሊዮን ሰዎችን የበከለ ሲሆን 3.5 ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል።












