"ወላይታን የጨቆነ ሥርዓት እንጂ ወላይታን የጨቆነ ብሔር የለም"

የፎቶው ባለመብት, EMNUEL
ጭቆናና በደል ወለደን ይላሉ። በወላይታ ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ግፍ አንገሽግሾ ወደ ፖለቲካ ጎትቶ እንዳስገባቸው ይናገራሉ። ከተመሠረተ ገና ሁለት ዓመቱ ነው። አማኑኤል ሞጊሶ፤ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን) ሊቀመንበርን በቁልፍ የወላይታ ሕዝብ ጥያቄዎችና ታሪካዊ ዳራዎች ዙርያ አወያይተናቸዋል።
ብሶት ነው የወለደን የምትሉት ለምንድነው?
የወላይታ ሕዝብ ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለረዥም ዘመናት፣ እጅግ የረቀቀ ዲሞክራሲያዊ ሊባል የሚችል ንጉሣዊ ሥርዓትና ዘመናዊ አስተዳደር የነበረው ሕዝብ ነው።
ይህ ሕዝብ ዘመናዊ ኢትዮጵያን በኃይል ከተቀላቀለ ጀምሮ ለኢትዮጵያ አንድነትም ሉአላዊነትም መስዋእትነትን የከፈለ ነው። የአገር ምሶሶ ሆኖ የዘለቀ ነው። ቢሆንም ለአገር ግንባታ ባበረከተው ልክ መጠቀም አልቻለም።
የአበርክቶቱን ያህል ተጠቃሚ አለመሆኑ አንድ ገፊ ምክንያት ነው።
በተለያዩ አካባቢዎች የወላይታ ተወላጆች ማንነታቸው ላይ ያነጣጠረ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ቁሳቂ ጥቃቶች እየደረሰባቸው መሆኑን ስናይ ይሄ ይሄ ተደማምሮ ነው ወደ ትግል ያስገባን።
ምን ያህል አባላት አሏችሁ?
የአባላት ቁጥር አሁን ለመናገር ያዳግተኛል። ግን በየቀኑ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።
እንደው አማካይ ቁጥር ሊሰጡኝ አይችሉም?
ውይ በጣም ብዙ ነው። እንዳላሳስትህ። እጄ ላይ አስተማማኝ መረጃ አልያዝኩም። ግን የዛሬን ብቻ ብንወስድ እኔ አሁን ባለሁበት ወረዳ ራሱ ከመቶ በላይ አባላት ተመዝግበዋል። ዛሬ አሁን ማለቴ ነው።
መቼስ እርስዎ ሊቀመንበር ኖት። በሪፖርትም በስብሰባም አባሎቻችሁ ስንት እንደደረሱ መጠቀሱ አይቀርብም ብዬ አስባለሁ። የሆነ ቁጥር ሊኖርዎ ይገባል።
ግርድፍ 'ዳታ' ንገረኝ ካልከኝ ወደ ግማሽ ሚሊዮን አባላት ይኖሩናል።
የተመዘገቡ፣ መዋጮ የሚያዋጡ 500ሺህ አባላት ነው አሉን ነው የሚሉኝ? አልበዛም?
ከዚህም በላይ ነው። እንዲሁ ግምት ነው የሰጠኹህ። መታወቂያ የወሰዱ፣ ፎርም የሞሉ፣ ሕጋዊ አባሎቻችንን ነው የምልህ።
ቅድም የወላይታ ታሪክ ተደፍጥጧል፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥም ተገቢው ቦታ አልተሰጠውም ሲሉኝ ነበር? የትኛው ታሪኩ ነው አልተነገረም የምትሉት?
ከ12ኛው አጋማሽ ጀምሮ ወላይታ ራሱን የቻለ አገር (State) ነበር። ሦስት ሥርወ-መንግሥታት (Dynasty) ነበረው። በነገሥታት የሚመራ ሕዝብ ነበር።
የራሱ የሆነ የምክር ቤት አወቃቀር ነበረው። የላይኛውና የታችኛው ምክር ቤት ተብሎ በእርከን የተከፋፈለ።
አብዛኛው ሕዝብ እቃ በእቃ እየተለዋወጠ ንግድ በሚያካሄድበት ዘመን ወላይታ የራሱ የሆነ መገበያያ (Currency) ነበረው። ስሙም 'ማርጯ' የሚባል ነበር። ብረት ቀልጦ የሚሠራ መገበያያ ነው። የ 'አይረን ኤጅ' ሥልጣኔ (Iron Age Civilization) የምንለው ነው።
ወላይታ በንግድ እስከ ሕንድ አገር ይገበያይ የነበረ ሕዝብ ነው። ግዛቱ እስከ ሸዋ፣ በደቡብ እስከ ኬንያ ቱርካና ሐይቅ ድረስ የነበረ ነው። እስከ ሕንድ ውቅያኖስ የሚዘልቅ የግዛት ቁጥጥር የነበረው ነው።
ወላይታ የራሱን መብት በማስከበርም በጦር መሣሪያ ብዙ ርቀት የሄደ ሕዝብ ነበር።
አቢሲኒያን ኢምፓየር በሚስፋፋበት ጊዜ አቢሲኒያዎች አብዛኛውን ቦታ ላይ በቀላሉ ሲቆጣጠሩ ወላይታ ላይ ለ7 ዓመት ነው ትግል የነበረው። ምን ያህል ጠንካራ አገር እንደነበረ ማየት ትችላለህ።
እንዴት ነው ታዲያ ከዚህ ገናና ታሪክ ተነስቶ በዞን የታቀፈ ሕዝብ ለመሆን የበቃው?
በዘመናዊ ኢትዮጵያ መፈጠር በኋላ በዚህ አገር የግዛት አንድነት እንጂ የሕዝቦች አንድነት ኖሮ አያውቅም። ይህ መሠረታዊ ሐሳብ ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ የፊውዳል ሥርዓት መጣ። በዚህ ሥርዓት ከአቢሲኒያ ውጭ ያለው የደቡቡን ክፍል 75 ከመቶ ገባር ያደረገ ነበር። ሌላው ጭሰኛ ነው።
ከቀን ወደ ቀን አንዱ አምርቶ ለሌላው እየሰጠ ለረዥም ዘመን የምርቱ ተጠቃሚ ባለመሆኑ ድህነት እየጨመረ መጣ። ማኅበረሰቡ ከአካባቢው ተፈናቀለ። ራሱን መመገብ አለመቻሉ የፈጠረው ነው።
ይህ በለም መሬት ላይ የነበረ ታታሪ ሕዝብ በጭቆና ምክንያት ራሱን መመገብ ተስኖት ወደ ከተማ መፍለስ አስገደደው። ሥርዓታዊ ጭቆና ነበረ የምንለውም ለዚሁ ነው።
የፊውዳሉ ሥርዓት ቀጥሎ ደርግ መጣ። ከዚያ ኢህአዴግ መጣ። ከዚያ ለውጥ ተባለና ደግሞ ቁጥር-2 ኢህአዴግ መጣ። በወላይታ ላይ የሚደርሰው ጭቆና ግን አልተገፈፈም።
ሥርዓታዊ ጭቆና ነው በወላይታ ሕዝብ የደረሰበት የምንለው ለዚህ ነው። የመዋቅር ጭቆና ነው ያለው።
ምንሊክ ኢትዮጵያን በአዲስ መልክ የመሥራቱን ፕሮጀክት እንዴት ነው የምትረዱት?
የምንሊክ እንቅስቃሴ የኃይል ነበር። አንድ መሆን ክፋት የለውም። አንድ የሆንበት መንገድ ነው ክፋቱ።
አብዛኛው ሰው ምንሊክ ኢትዮጵያን አንድ አድርገዋል ይላል። አንድ በማድረጉ፣ አንድ በመሆናችን ክፋት የለም። አንድ ከሆን በኋላ የሆነው ነው ክፋቱ።
ባሕል እንዲጠፋ ተደረገ። ቋንቋ ተጨፈለቀ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እኮ የደቡብ ሕዝቦች የራሳቸውን ቋንቋ ማውራት የሚያሸማቅቅ ነበር።
ኢትዮጵያ 'ባሕለ ብዙህ' ናት። ነገር ግን ወደ "አንድ ዓይነትነት" ለማምጣት መሞከሩ ነው አደጋው።
ስለዚህ ምንሊክ የግዛት አንድነት እንጂ የሕዝቦችን አንድነት አልፈጠሩም። የበላይና የበታችን ነው የፈጠሩት። ከዚያ በኋላ የመጣውም ሥርዓት ይህንኑ ነው ያስቀጠለው።
ሁሉንን የምታንጸባርቅ ኢትዮጵያን ካልፈጠርን ደግሞ የሕዝቦች አንድነት ሊመጣ አይችልም። በፍጹም። ትግሉም እስከዛሬ የቀጠለው ለዚሁ ነው።
የአፄ ምንሊክ "የኢትዮጵያ ፕሮጀክት" በዚህ መንገድ ተጨናግፏል የምትሉ ከሆኑ የተጨናገፈው የቱ ጋ ነው? የርሳቸው ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ስህተቱ ምኑ ላይ ነው?
የሕዝቦችን አንድነት ማምጣት አለመቻላቸው ነው ትልቁ የርሳቸው 'ፌይለር'። የግዛት አንድነት ነው የፈጠሩት።
የግዛት አንድነት መፍጠራቸው ችግር አልነበረውም። በሕዝቦች አንድነት መረጋገጥ ግን ነበረበት። ከሳቸው በኋላም ይህ አልሆነም።
ያ ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ፣ ቋንቋችን፣ ታሪካችን፣ ባሕላችን ባይታቀብ ኖሮ፣ የበታችና የበላይ የሚባል ባይኖር ኖሮ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የነበረው እንቅስቃሴና ትግል ሁሉ ባልኖረ ነበር።
ምንሊክ በግድም በውድም የግዛት አንድነት ከፈጠሩ በኋላ ሁሉም በአካባቢው እየገበረ ይነስም ይብዛ ራሱን እንዲያስተዳደር መሞከራቸው ተራማጅ አያሰኛቸውም? ቢያንስ በጊዜው መለኪያ ማለቴ ነው።
አይ! እሱን እንኳ ብንተወው ነው የሚሻለው።
እንኳንስ ያኔ አሁን እኮ በክልሎች ሰዎች ይሾማሉ። የመወሰን ሥልጣን ግን የላቸውም።
በእውነተኛ ፌዴራሊዝም ሕዝቦች መሪያቸውን ራሳቸው ናቸው የሚመርጡት።
በኢትዮጵያ ግን ሥልጣን ለሕዝቦች ተሰጥቶ አያውቅም። ባለሥልጣን ከማዕከል ነው የሚላክልህ። ድሮም አሁንም። ሰጪም ነሺም ማዕከላዊ መንግሥት ሆኖ ነው የቀጠለው።
ፓርቲያችሁ ለወላይታ ሕዝብ መብቶች ብቻ መታገሉ በታላቋ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ውክልናችሁ አልጠበበም ወይ?
ፓርቲያችን ለወላይታ ሕዝብ የቆመ ፓርቲ ነው። ይሁን እንጂ ፓርቲያችን የቃል ኪዳን ሰነድ (ማኒፌስቶ) ላይ በግልጽ እንዳስቀመጥነው ወላይታነት ከእናትና ከአባት የሚወረስ የደም ውርስ አይደለም።
ወላይታነት የአስተሳሰብ ዝንባሌ ነው። ባሕሪ ነው።
እንዴት ማለት? አልገባኝም።
ጥሩ! የወላይታን ማኅበረሰብ ቋንቋውን፣ ባሕሉን፣ ልማቱን፣ ደግፎ ለቋንቋው ዕድገት የሚሠራ፣ በተግባር ለዚህ ማኅበረሰብ ለውጥ የሚተጋ የሚታገል የአስተሳሰብ ዝንባሌ ያለው ማለታችን ነው።
አንድ ሰው በደም ወላይታ ስለሆነ ብቻ፣ አባትና እናቱ ወላይታ ስለሆኑ ብቻ ወላይታነቱን ያሟላል ማለት አይደለም። ያ ከሆነ የዘር ጉዳይ ነው የሚሆነው። ለዚህ ነው ወላይታነት የአስተሳሰብ ዝንባሌ ነው የምንለው።
አንድ ሰው ወላይታ ለመሆን ግዴታ አጥንትና ደሙን አንቆጥርም። ወላይታ አይደለም ብለን አናገልም።
እዚህ አካባቢ ለምሳሌ ረዥም ዓመት የኖሩ፣ የተዋለዱ የወላይታን ልማድ ቋንቋ የሚደግፉ የተለያዩ ብሔሮች አሉ። እነዚህ ለኛ ወላይታዎች ናቸው። አካታች ነን ነው የምልህ።
የዘውግ ፓርቲ አይደለንም እያሉኝ ነው?
ይኸውልህ። ችግሩ ይሄ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፖለቲካን ለማጥላላት ብዙ ስም ይሰጡታል። የዘውግ ፖለቲካ ይሉታል፤ የዘር ፖለቲካ ይሉታል። የጎሳ ይሉታል። ጨፍላቂዎች ናቸው ይህን የሚሉት።
ብሔር፣ ዘውግና ዘር በመሠረታዊነት የተለያዩ ነገሮች ናቸው።
ብሔር ማለት የራሱ ቋንቋ ያለው። የራሱ ግዛትና አስተዳደር መዋቅር ያለው፣ የጋራ ሥነ ልቦና ያለው፣ ይሄን ነው ብሔር የምንለው።
ብሔሮች ለመብታቸው እንዳይታገሉ ሲፈልጉ ጨፍላቂዎች የዘር ፖለቲካ ወይም የዘውግ ፖለቲካ እያሉ ለማንቋሸሽ ይሞክራሉ። ፍጹም ስህተት ነው።
ብሔርን አሸማቀህ ልታጠፋው አትችልም።
የኛ ፖለቲካ የዘርም የጎሳም አይደለም። የኛ ፖለቲካ ሁሉም ብሔሮች በፖለቲካም በኢኮኖሚም በእግራችን ልክ ጫማ ማድረግ አለብን ብሎ የተነሳ ጥያቄ ነው።
መሠረታችን ወላይታ ነው፤ መዳረሻችን ግን ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የምትመች እኩል የሆነች ኢትዮጵያን መገንባት ነው።
እሺ! ዘውግ፣ ብሔር፣ ዘር፣ ጎሳ ምንድነው የሚለውን ለጊዜው እናቆየውና ቅድም ያነሱትን ሐሳብ አንስቼ ልሞግትዎ። ማንኛውም ሰው አጥንትና ደሙ ወላይታ ስለሆነ ብቻ ወላይታነትን አያሟላም ብለውኛል። በአንጻሩ ማንኛውም ሰው በደሙ ወላይታ ባይሆንም በአስተሳሰብ ዝንባሌውና ባሕሪው ወላይታነትን ከተላበሰ ወላይታ ነው ብለውኛል። እንበልና ክልል ብትሆኑ፣ ይህን የሚሉትን የአስተሳሰብ ዝንባሌ የሚያሟላ አንድ ጉራጌ የክልላችሁ ፕሬዝዳንት ሊሆን ይችላል?
እዚህ ጋ ምናለ መሰለህ? እኛ የምናስበው፣ ሕዝቡ እዚህ ወላይታ አካባቢ አብላጫ ድምጽ ያለው ሕዝብ ድምጽ እንዲኖረው እንፈልጋለን። ውክልና እንዲኖረው እንታገላለን።
እኛ አካታች ነን ስንል እዚህ አካባቢ ያለ እኩል ከኛ ጋር የታገለ ሕዝብ ተገቢውን ውክልና እንዲያገኝ እናደርጋለን ማለታችን ነው።
ወላይታ አካባቢ ስንታገል የአብላጫውን ድምጽ ነው የምናከብረው።
ወላይታ አካባቢ ላይ አብዛኛው ሕዝብ ወላይታ ብሔር ነው። ስለዚህ ሌላው ብሔረሰብ በቁጥሩ ልክ የመሳተፍ ዕድል ይኖረዋል እያልኩህ ነው። በዚህ አግባብ ነው የምንሄደው።
ዜግነት ፖለቲካን እንዴት ነው የምትረዱት። ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትንስ?
ሲጀመር ኢትዯጵያ ሕብረ ብሔራዊ ናት። ኢትዮጵያ ብሔርተኝነት የሚባል ነገር ሊኖርም አይችልም።
ኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ሊኖር ይችል የነበረው ከ60 እና ከ70 ከመቶ አብላጫ የሆነ አንድ ብሔር ቢኖር ነበር።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውም ብሔር ያንን መስፈርት አያሟላም።
ኢትዮጵያን ሕብረ ብሔራዊ መሆኗን መካድ አንችልም። አፈጣጠራችን ነው።
አንድነትን ለማምጣት በሚል ሕዝቦችን የመቀየር፣ ባሕላችንን የመቀየር ትግል ውስጥ መግባት የለብንም።
ብሔር ብሔረሰቦችን ይዘን ነው አገር ልንገነባ የምንችለው። በእውነተኛ ፌዴራሊዝም ነው ኢትዮጵያ ዳግም የምትፈጠረው።
ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ፌዴራሊዝም አስተዳደርን መቃረን ነው እንዴ?
እርግጥ ነው ሁሉም ፓርቲ ፌዴራል ሥርዓት ነው የምገነባው ይልሃል። ዋናውን መስፈርት ግን ይረሱታል።
ምንድነው ያ መስፈርት?
ፌዴራሊዝም ራስን ማስተዳደር ማለት ነው። እንዴት ነው ፌዴራላዊ ሥርዓት የምትገነቡት ስትላቸው አንዳንዶቹ ኢትዮጵያን ለ5 እንከፍላታለን ይሉሃል።
አንዳንዶቹ ገና እያሰብንበት ነው ይሉሃል።
በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ላይ ሙከራ (Experiment) ለመሥራት የተዘጋጁም አሉ።
ጭራሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔር የለም የሚሉም አሉ።
በጥቅሉ ካየኸው ግን አገራዊና ዜግነታዊ ፖለቲካ ነው የምናራምደው የሚሉ ፓርቲዎች የምዕራብ ማኒፌስቶ ነው ሊጭኑብን የሚሞክሩት።
ምን ማለት ነው ይሄ?
ምን ማለት ነው፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ትንሽ ከተቀረፉልን፣ ስለታሪክ፣ ስለባህል ምናምን መጨነቅ አያስፈልግም።
ባህል ቅብርጥሶ ከሆነ ጊዜ በኋላ ቢጠፋም ባይጠፋም አይጨንቀንም ይሉሃል።
ከበላህ፣ ከጠጣህ በቂ ነው፤ እሴትህ ባሕልህ ምናምን እኛ አያገባንም ይሉሃል። እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች ከፊውዳሉ ሥርዓት በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ብዙም አይለዩም።
እውነተኛ ፌዴራሊዝም እነሱ ጋ የለችም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዜግነት ፖለቲካ ለተሰባሰቡ ቡድኖች የተመቹ ናቸው ይሏቸዋል፤ አያያዛቸውን በማየት። እሳቸው በሂደት ፌዴራላዊ መዋቅሩን ሊያጠፉና አንድ ሕዝብ ለመፍጠር ሊሞክሩ ይችላሉ ብላችሁ ትሰጋላችሁ?
በግለሰብ ደረጃ ስም ማንሳት አልወድም። እንደ ሥርዓት ነው ማየት የምፈልገው። አንድን አገር በአንድ ግለሰብ ጭንቅላት ብቻ ትፈጠራለች ብሎ ማሰብ አዝማሚያው በራሱ አደገኛ ነው።
በወላይታ ሕዝብ ላይ ጭቆና ያደረሰ ብሔር አለ ብላችሁ ታምናላችሁ?
ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳኸልኝ። በኢትዮጵያ በመሠረታዊነት ያለመረዳት ያለው በዚህ ነጥብ ዙርያ ነው።
ጨቋኝ ሥርዓትንና ብሔርን አንድ አድርጎ የማየት ነገር አለ።
ጨቋኙ ሥርዓት በብዛት የወጣበት አካባቢ ለምሳሌ አማራው ወይም ትግራዩ ወይም በአጠቃላይ አቢሲኒያውን ጨቋኝ ነበርክ ይሉታል።
የአሁን ፖለቲከኞች ይህንን ለፖለቲካ ፍጆታ ይጠቀሙበታል።
እኛ እንደ ወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ወላይታን የጨቆነ ሥርዓት እንጂ ወላይታን የጨቆነ ብሔር የለም ብለን ነው የምናምነው።
ወላይታ ላይ የደረሰው ሁለት ዓይነት ጭቆና ነው። አንደኛው ሥርዓታዊ ነው፤ ሁለተኛው መዋቅራዊ ነው።
ሥርዓቱ ያመጣው መዋቅር አለ። ያ መዋቅር ወላይታ ራሱን በራሱ እንዳያስተዳድር መብቱን ነሳ።
ይኸው ነው። ዛሬም ድረስ የቀጠለ ነው ይሄ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለምድነው የወላይታ ልጆች ትምህርት ቤት መሄድ ትተው ወደ ከተሞች በብዛት እየመጡ ያሉት? አዲስ የተፈጠረ ነገር አለ?
በወላይታ የሕዝብ ለመሬት አሰፋፈር ጥግግቱ (Population Density ration) በኢትዮጵያ ከፍተኛው ነው።
በጠባብ መሬት ብዙ ሰው ይኖራል። ወደ ገጠር ስንሄድ በከተሞች ሕዝቡን የሚመግብ ኢኮኖሚ ስለሌለ እዛው ያቺኑ መሬት ከቦ ነው የሚቀመጠው።
ገጠር ላይ በዚያችው መሬት እንዲቆይ የሚያስችለው የእርሻ ሥራና ምርት ከሌለ ያለው አማራጭ መሰደደ ነው።
ገጠር ገብተህ ብትጠይቃቸው ይነግሩሃል። አርሶ አደሩ ምን እንደሚል ታውቃለህ? 'መሬቱን ጠይቀው ይናገራል' ይልሃል።
ያቺው መሬቱን በተደጋጋሚ ሲያርሳት ለምነቷ ተንጠፍጥፎ አልቋል። የልጅ ልጅ ልጆቹ የሚቀበላቸው ኢንዱስትሪ በአካባቢያቸው የለም።
ታዲያ ከመሰደድ ውጭ ምን ያድርጉ?
ከሲዳማ ክልል መሆን በኋላ የወላይታ እየተጠበቀ ጥያቄው ተፋፍሞ ሳለ ድንገት ከሰመ። ምን ሆነ?
ሐቀኛ የሕዝብ ተወካይ የለም። ሐቀኛ የሕዝብ ውክልና የለም። አሁን ያለው አመራር የሕዝብ ጥያቄን ቀልብሶ ነው በሥልጣን ያለው።
ይሄ ምርጫ ለወላይታ የሕልውና ምርጫ ነው የምንለው ለዚህ ነው።
የሲዳማን ጥያቄ የመለሰ፣ የወላይታን ጥያቄ የቀለበሰ መዋቅር ምን ልትለው ትችላለህ? ለኛም 'አብስትራክት' ነው የሆነብን።
ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ የሲዳማን ጥያቄ ተከትሎ የመጣ አይደለም። ከጦና ጊዜ ጀምሮ የነበረ ነው። 150 ዓመታት ያለፈው ጥያቄ ነው።
ታሪካዊና ሞራላዊ እና ሕገመንግሥታዊ ጥያቄ ነው። ሊመለስ የሚገባው ነበር። የሥርዓቱ ጨቋኝነት፥ የሥርዓቱ ኢፍትሐዊነት፣ ሐቀኛ ተወካይ ማጣት መልስ እንዳናገኝ አድርጎናል።
አሁን በምን ሁኔታ ነው ያለው ታዲያ?
ሕዝቡ ጥያቄው አጥንቱ ውስጥ ገብቷል። ጥያቄውን ይህ ትውልድ ይዞ ይቀጥላል።
ለጭቆናችን መሠረት የሆነውን መዋቅር ሳናስተካክል የሚቃና ነገር የለም። ጥያቄው የፖለቲካ ነው። በፖለቲካ አደረጃጀት ነው መመለስ ያለበት። የተደራጀነውም ለዚሁ ነው።
አሁን ያለው የዐቢይ አስተዳደር በብዙ ነገሮች ተወጥሮ ያለ ነው። በዚህ ወቅት የክልል እንሁን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው? ክልል መሆንስ መሠረታዊ ጥያቄን ይፈታል ወይ? ወረዳ፣ ዞን ስለሆነ፥ ዞን ክልል ስለሆነ ለሕዝብ ጠብ የሚል ነገር ይመጣል?
ጨፍላቂ አስተሳሰብ ነው የምልህ ይህንን ነው።
ወረዳን ዞን የማድረግ ምናምን አይደለም ነገሩ። 56 ብሔር የተጨፈለቀበት መዋቅር የወላይታን ልማት ሊያረጋግጥ አይችልም። አንድ ብሔር ራሴን ላስተዳድር ሲል የሚከለክል ሥርዓት ጨቋኝ ሥርዓት ነው።
ጭቆናውም የብሔር ጭቆና ይባላል። አንድ ብሔር ብሔር ከሚያሰኙት ነገሮች አንዱ ራሱን ማስተዳደር መቻሉ ነው።
'ኢህአዴግ -ቁጥር-2' ከመጣ ሦስት ዓመት አለፈ። ሁልጊዜ የደቡቡን ጥያቄ ወደታች ነው የሚቀብሩት።
ቅደም ተከተል ላይ ይገፉታል። ሦስት ዓመት ሙሉ 'አሁን ጊዜው አይደለም' ሲባል ነበር። የሚቀጥሉት ዓመታትም ጊዜው አይደለም ይሉናል።
የወላይታ ጥያቄ ብቻ አይደለም እኮ ግን። 56ቱንም በደቡብ የሚገኙ ሕዝቦችን ብንጠይቅ እርስዎ ያሉትን ይሉናል።
እንኳንም አነሳኻው ይህን ጥያቄ። በደቡብ የተሠራውን ሸፍጥ ልንገርህ።
የወላይታ ጥያቄ እንዳይመለስ ጭራሽ ጥያቄው ውልብ ብሎባቸው የማያውቁ ሕዝቦችን ሁሉ በር እያንኳኳ ክልልነት ጠይቁ ነው የተባሉት።
የወላይታን ጥያቄ ለማዳፈን ሆን ተብሎ የተሠራ ሸፍጥ ነው።
ስለዚህ የክልልነት ጥያቄ ጊዜው አሁን ነው ብለው ያምናሉ?
ምን ዓይነት ጥያቄ ነው ይሄ? 50 እና 60 ዓመት የቆየ ጥያቄ እኮ ነው።
ለምንድነው ጊዜው አይደለም የምትለኝ? ጊዜው አሁን ካልሆነ መቼ ነው ታዲያ? ለዚህ ሁሉ ዓመተ ጥያቄው መታፈኑ አይመስልህም ይህን ሁሉ ቀውስ ያመጣው?












