የቺሊ ብሔራዊ ቡድን ሊሰልለኝ ነበር ያለውን ድሮን ቢጥልም ስህተት መሥራቱ ታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሩጫው የስፖርት መስክ ኢትዮጵያና ኬንያ ተቀናቃኞች እንደሆኑት ሁሉ የደቡብ አሜሪካ አገራት የሆኑት ቺሊና አርጀንቲና ደግሞ ለዘመናት በእግር ኳስ ውድድር ተቀናቃኝነታቸው ይታወቃሉ።
ለዚህም ነው ሁለቱ አገራት ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዛሬ ሐሙስ ከሚያደርጉት ግጥሚያ ቀደም ብሎ የቺሊ ብሔራዊ ቡድን ልምምድ በሚያደርግበት ሜዳ ላይ አንዲት ድሮን ስታንጃብብ ጥርጣሬ የተፈጠረው።
በዚህ ጊዜ የቺሉ ቡድን የገመተው አርጀንቲናውያኑ ተቀናቃኞቻቸው ድሮን አሰማርተው እየሰለሏቸው እንደሆነ ነበር። በምላሹም የእራሳቸውን ድሮን ልከው "ሊሰልለን መጥቷል" ያሉትን ድሮን በቁጥጥር ስር አዋሉት።
ነገር ግን ድሮኑ እነሱ እንደጠረጠሩት የአርጀንቲናውያን ሳይሆን የአንድ የአገራቸው የኃይል አቅራቢ ኩባንያ ንብረት ሆኖ አግኝተውታል።
ይህ የተከሰተው ቺሊና አርጀንቲና ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ሐሙስ ዕለት ከሚያደርጉት ጨዋታ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ነበር።
የቺሊ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ለዛሬው ውድድር ለመዘጋጀት በዋና ከተማዋ ሳንቲያጎ ውስጥ በሚገኝ ስታዲየም ልምምድ እያደረጉ ሳለ ነበር "የስለላ" ነው ያሉት ድሮንን የተመለከቱት።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት የቡድኑ አሰልጣኝ ማርቲን ላዛርቴ ናቸው የአጠራጣሪውን ድሮን ምንነት ለማወቅ የራሳቸውን ድሮን በማብረር እርምጃ የወሰዱት።
በዚህም ሁለቱ ድሮኖች አየር ላይ ተጋጩ በስፍራው የነበሩ ጋዜጠኞች እንደተናገሩት ሆን ተብሎ የተፈጠረ ግጭት ነበር።
በዚህም ሰላይ የተባለው ድሮን ወደ መሬት ወደቀ። ሲጣራም ድሮኑ አርጀንቲናውያን የቺሊን ብሔራዊ ቡድን ለመሰለል ያሰማሩት ሳይሆን 'ኤኔል' የተባለው ኩባንያ በአካባቢው ለሥራ ያሰማራው እንደሆነ ተደረሰበት።
በድሮን አማካይነት በእግር ኳስ ቡድኖች ላይ የሚደረግ ስለላን በተመለከተ ሲነገር ይህ የመጀመሪያው አይደለም። አሰልጣኞችም በዚህ ዙሪያ ቀደም ሲል ቅሬታ አሰምተዋል።
ከእነዚህም መካከል ከስድስት ዓመታት በፊት የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበረው ዲዲየ ዴሾ ብራዚል ውስጥ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ወቅት ቡድኑ ከሆንዱራስ ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ በፊት በልምምድ ስፍራ ላይ ሲንዣብብ የነበረን ድሮን በተመለከተ ፊፋ ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቆ ነበር።
በተመሳሳይ እአአ 2017 ላይ ሆንዱራስ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በምትዘጋጅበት ጊዜ አውስትራሊያ ድሮን አሰማርታ ቡድኔን እየሰለለች ነው በማለት ክስ አቅርባ ነበር። በተጨማሪም ቡድኑ ክስተቱን የሚያሳይ ቪዲዮ በትዊተር ላይ አሰራጭቶ ነበር።
ከአገራት ብሔራዊ ቡድኖች በተጨማሪም ታላላቅ ክለቦች ተመሳሳይ ነገር እንዳጋጠማቸው ተነግሯል።
የጀርመኑ ወርደ ብሬመን ክለብ ከሦስት ዓመት በፊት በተቀናቃኙ ሆፈንሃይም ቡድን የልምምድ ሜዳ ላይ ድሮን እንዲያንዣብብ ማድረጉን አምኖ ለድርጊቱ ይቅርታ ጠይቆ ነበር።
አሁን አሁን በድሮን አማካይነት በቡድኖች ላይ የሚደረግ ስለላን በተመለከተ የሚቀርቡ ክሶች እየተለመዱ የመጡ ሲሆን፤ አንዳንድ የቡድን አሰልጣኞች ግን አሁንም የቆየውን ተቀናቃኞቻቸውን የመሰለል መንገድን እየተጠቀሙ እንደሆነ ይነገራል።
ከሁለት ዓመት በፊት በአውሮፓውያኑ 2019 የእንግሊዙ ሊድስ ዩናይትድ ዋና አሰልጣኝ ማርሴሎ ቢየልሳ ተቀናቃኛቸው የሆነውን ደርቢ ካውንቲ እንዲሰልልላቸው አንድ የቡድኑን አባል ወደ ልምምድ ሜዳ መላካቸውን ተከትሎ ቡድኑ ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, AFP












