ተቃዋሚዎች 'ስላቅ' ነው ያሉት ምርጫ በሶሪያ እየተካሄደ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሶሪያ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች ላይ እየተደረገ ባለው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በሽር አል አሳድ ለ4ኛ ጊዜ ለ7 የስልጣን ዓመታት ለመምራት አሸናፊ እንደሚሆኑ እርግጥ እየሆነ ነው።
የፕሬዝዳንት አሳድ ተፎካካሪዎች ሆነው የቀረቡት ብዙም የማይታወቁ አብደላ ሳልሙንና ማህመድ አህመድ የተባሉ ፓለቲከኞች ናቸው።
ምርጫው ከተካሄደባቸው በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ አካባቢዎችን የተቆጣጠሩ ተቃዋሚዎች ምርጫውን ቀልድ ነው ያሉት ሲሆን የአሜሪካና አውሮፓ ፓለቲከኞች ደግሞ ፍትሀዊና ነፃ ያልሆነ ምርጫ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ፕሬዝዳንት አሳድ ድምፃቸውን በሰጡበት ወቅት በሰነዘሩት አስተያየት የምዕራባውያን አስተያየት "ዜሮ" ተብሎ ተቆጠረ ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ የዘመን ስሌት በ2011 ዲሞክራሲን እንፈልጋለን ያሉ ተቃዋሚዎች ላይ የበሽር አል አሳድ መንግስት የኃይል እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ የተቀሰቀሰ ግጭት 10 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ሶሪያን 'እንዳልነበረች' አድርጓታል።
የ55 ዓመቱ በሽር አል አሳድ እንደ አውሮፓውያኑ 2000 ላይ ነበር ከሩብ ምዕተ ዓመት ለሚልቅ ጊዜ ሀገሪቱን የመሩትን አባታቸውን ተክተው ፕሬዝዳንት የሆኑት።
ከሰባት ዓመታት በፊት ሀገሪቱ በግጭት ውስጥ ሆናና ተቃዋሚዎች ለመሳተፍ ባልተስማሙበት ምርጫ ፕሬዝዳንት አሳድ 88 በመቶ የሚሆነውን ድምፅ በማሸነፍ ለ3 ጊዜ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠው ነበር።








