ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በስፔን ጠፍቶ የነበረ ግለሰብ አስከሬን በዳይኖሰር ሐውልት ውስጥ ተገኘ
ስፔን ውስጥ ጠፍቶ የነበረ አንድ ግለሰብ አስከሬን በዳይኖሰር ሐውልት ውስጥ መገኘቱን ፖሊስ አስታወቀ።
የስፔን ፖሊስ በዳይኖሰር ሐውልት ውስጥ የ39 ዓመት ግለሰብ አስከሬን ማግኘቱን ተከትሎ ምርመራ ማድረግ ጀምሯል።
አስከሬኑ ሊገኝ የቻለው እሁድ ዕለት በአካባቢው የነበሩ አባትና ልጅ ባርሴሎና ከሚገኘው የዳይኖሰር ሐውልት ውስጥ የሚመጣው ጠረን ባሳደረባቸው ጥርጣሬ ነው።
ጥርጣሬ የገባቸው አባትም በሐውልቱ ሽንቁር ውስጥ ሲያጮልቁ አስከሬን ተመልክተው፤ ጉዳዩን ለአካባቢው አስተዳደር አመልክተዋል።
ፖሊስ እንዳለው በሐውልት ውስጥ ሞቶ የተገኘው ግለሰብ ከዚህ ቀደም ቤተሰቦቹ ጠፍቶብናል ብለው አመልክተው ነበር።
ሆኖም ግን እስካሁን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው እንደሌለ ፖሊስ ገልጿል።
በሐውልት ውስጥ አስከሬን መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች በሥፍራው ተገኝተው በዳይኖሰር ምስል ቅርጽ የተሰራውን የሐውልቱን እግር በመክፈት አስከሬኑን አውጥተውታል።
እንደ ስፔን የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ይህ በስም ያልተጠቀሰው ግለሰብ የእጅ ስልኩን ከሐውልቱ ውስጥ ለማውጣት ሲጥር ወደ ውስጥ እንደወደቀና የድረሱልኝ እርዳታ ጥሪ ማሰማት ባለመቻሉ ሐውልቱ ውስጥ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል።
ይሁን እንጅ የግለሰቡን ሞት ምክንያት ለማረጋገጥ የአስከሬን ምርመራ ውጤት እየጠበቀ የሚገኘው ፖሊስ፤ ይህንን በመገናኛ ብዙሃን የተለጸውን የግለሰቡን አሟሟት ትክክለኛነት አላረጋገጠም።
የቀድሞ ሲኒማን ለማስተዋወቅ ይውል የነበረው የዳይኖሰር ሐውልት ከነበረበት አካባቢ እንዲነሳ ተደርጎ ነበር።