የ23 ዓመቷ የአሳ ነጋዴ በእድሜ ትንሿ የኡጋንዳ ፓርላማ አባል ሆነች

የ23 አመቷ የዓሳ ነጋዴ
ታትሟል

ባለፈው ጥር በኡጋንዳ በተካሄደው ምርጫ የገዢው ኤን አር ኤም ፓርቲ አባል የሆነችውና በቅርቡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው የ23 ዓመቷ ሄለን አውማ ዋንዳራ በተወዳደረችበት አካባቢ አሸንፋለች።

በምስራቃዊ ኡጋንዳ የቡስሪያ አውራጃን ወክላ ለሴቶች ከተያዙ መቀመጫዎች አንዱን ማሸነፏን ያረጋገጠች ተመራጯ በስራ ላይ ያለ በእድሜ ትንሿ የፓርላማ አባል ትሆናለች።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ከማጠናቀቋ በፊት እናቷ በሚሰሩበት የአሳ ንግድ ላይ ትሰራ እንደነበር ዴይሊ ሜል ጋዜጣ ዘግቧል። አሳዎቹን እየጠበሰች ለኮሌጅ ጓደኞቿም ትሸጥ ነበር።

አስተያየቷን ለጋዜጣው ስትሰጥ "በፈጣሪ መመሪያ" ነው ወደ ፖለቲካው የተቀላቀልኩት ብላለች።

የፓርቲው አባላት 'እማማ ቡሱኒያ' [ቡስኒያ የተወዳደረችበት አውራጃ ነው] እያሉ የሚጠሯት አውማ በሞተር ሳይክልና በየቤቱ በመዞር የምርጫ ቅስቀሳ ስታደርግ ነበር።

የተወዳደረችለት ኤን አር ኤም ፓርቲ የፓርላማ ተመራጯ አውማ ወደ ፖለቲካ ለመግባት ያለፈችበትን የህይወት ጉዞ የሚያሳይ ቪዲዮ ባለፈው ወር አጋርቶ ነበር።

ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ የፓርላማ ተመራጮች ቃለ መሃላ እየፈጸሙ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናትም የሚቀጥል ይሆናል።

በኡጋንዳ ታሪክ በትንሽ እድሜ ፓርላማን የተቀላቀለችው አሌንጎት ኦሮማይት የተባለች አባል ስትሆን እንደ አውሮፓውያኑ በ2011 የፓርላማ አባል ሆና ስትመረጥ 19 ዓመቷ ነበር።