አትሌቲክስ ፌደሬሽን፡ 'በኦሊምፒክ የሚሳተፉ ሯⶐች የሚመረጡት በቴክኒክ ኮሚቴ ነው' አለ

ታትሟል

በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው በማራቶን የሚወደዳሩ አትሌቶችን የሚመርጠው ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲሆን ከስምምነት መደረሱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ በኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝደንት በሆኑት አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የሚመራ ሲሆን የአትሌቲክስ አሰልጣኞች የኮሚቴው አባላት ናቸው።

ይህንን በሚመለከት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዛሬ ማክሰኞ መግለጫ ሰጥቷል።

የዛሬው መግለጫ የአትሌቲክ ፌዴሬሽን፣ የኦሊምፒክ፣ የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን እና ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር በጋራ ይሰጣሉ ተብሎ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን መግለጫ የኢትዮጵያ አትሌቲክ ፌዴሬሽን ብቻ እንዲሰጥ ከስምምነት መደረሱ በመግለጫው ተጠቅሷል።

አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሚያዚያ 23 በሰበታ ከተማ በተካሄደው የማራቶን ማጣሪያ ውድድር የተሻለ ሰዓት ያስመዘገቡ አትሌቶችን ይፋ አድርጎ እንደነበረ ይታወሳል።

ለቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በተካሄደው ማጣሪያ ከ1 እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት አትሌቶች ሹራ ቂጣታ፣ ሌሊሳ ዴሲሳ፣ ሲሳይ ለማ እና ጫሉ ዳሶ መሆናቸው ይታወሳል። በሴቶች ደግሞ ትዕግስት ግርማ፣ ብርሀኔ ዲባባ፣ ሮዛ ደረጄ እና ዘይነባ ይመር የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።

ፌዴሬሽኑ የማራቶን ተሳትፎ በቴክኒክ ኮሚቴው የሚወሰን ነው ከማለት ውጪ ሰበታ ከተማ ተካሂዶ በነበረው ማጣሪያ ውጤታ ያስመዘገቡ አትሌቶች እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ያለው ነገር የለም።

በሌላ በኩል ይህ ማጣሪያ አግባባ አይደለም በማለት አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በማጣሪያው ላይ ሳይሳተፍ መቅረቱ ይታወሳል።

አትሌት ቀነኒሳ 2016 በተካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክ ተሳታፊ እንዳልነበር አስታውሶ፤ በኦሊምፒክ መድረክ አገሬን እንዳልወክል በፌደሬሸኑ እየተከለከልኩ ነው ሲል ቅሬታ አቅርቦ ነበር።

በማራቶን የሚወዳደሩ አትሌቶችን በተመለከተ የቴክኒክ ኮሚቴው ውሳኔ ወደፊት ይፋ እንደሚደረግም ተነግሯል።

በሌላ በኩል ከ800 ሜትር እስ 10ሺህ ያሉ ወድድሮች ኢትዮጵያ ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶችን ለመምረጥ 73 አትሌቶችን የሚያሳትፍ ማጣሪያ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

ይህ የማጣሪያ ውድድር በስዊትዘርላንድ ሄንግሎ ከተማ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ እንደሚካሄድና ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ብቻ የሚያሳትፍ መሆኑም ተጠቅሷል።

በዚህ መሠረት በሄንግሎ በሴቶች እና በወንዶች የ800፣ 1ሺህ 500፣ 3ሺህ፣ 5ሺህ እና 10ሺህ ሜትር ማጣሪያዎች ይከናወናሉ።