ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቶኪዮ ኦሊምፒክ፡ አውስትራሊያ የኦሊምፒክ ተሳታፊዎችን ለማስተዋወቅ የለቀቀችው ፎቶ አወዛገበ
የአውስትራሊያ ኦሊምፒክ ቡድን ተወዳዳሪዎችን ለማስተዋወቅ የለጠፈው ፎቶ ውግዘት ገጥሞታል።
የአውስትራሊያን የኦሎምፒክ ቡድን ለማስተዋወቅ ይፋ የተደረገው ፎቶ ብዝሃነትን አያንጸባርቅም በሚል አንዲት ጥቁር ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ራሷን ከውድድሩ ልታቅብ እንድምትችል አስጠንቅቃለች።
የአውስትራሊያን የኦሊምፒክና ፓራሊምፒክ [የአካል ጉዳተኞች የሚሳተፉበትን] ተሳታፊዎች ትጥቅን ለማስተዋወቅ የተለቀቀው ምስል ላይ የሚታዩ ሰዎች በሙሉ ተመሳሳይ የቆዳ ቀለም ያላቸው ናቸው።
እናም በሀገሪቱ እውቅና ያላት ጥቁር የቅርጫት ኳስ ተጫዋቿ ሊዝ ካምቤጅ ፎቶውን “ነጭ የተቀባ” ብላዋለች።
የኦሎምፒክ ቡድኑን ብዛሃነትን ለማንጸባርቅ ከዚህ የተለየ ነገር መስራት ነበረበት ያለው ደግሞ የአውስትራሊያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ነው።
በ2012 ኦሊምፒክ የነሀስ ሜዳሊያ ያገኘችው ካምቤጅ ጉዳዮ ቅር እንዳሰኛት መጀመሪያ የገለጸችው በኢንስታግራም ገጿ ነበር።
ናይጄሪያዊ አባትና አውስትራሊያዊት እናት ያላት ቅርጫት ኳስ ተጫዋቿ የተወለደችው ለንደው ውስጥ ነው።
ይህ አነጋጋሪ ምስል ማሕበራዊ ድር አምባ ላይ ሲለጠፍ ከስሩ የተቀመጠው የመጀመሪያው አስተያየት “እኔን የማይወክልኝ ሀገርን እንዴት ሊወክል ይችላል?” ሲል ይጠይቃል።
ከዚህ በፊት የአውስትራሊያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች የቡድኑ ማልያ በሴቶች ልክ የለም መባሉን ተከትሎ ቁጣቸውን አሰምተው ነበር።
የሃገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለወንዶች ያደላል ተብሎም የማሕበራዊ ድር አምባ ግርግር ተነስቶ ነበር።