በኢንዶኔዥያ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ የኮቪድ ናሙና መሰብሰቢያዎችን በድጋሚ የተጠቀሙ ግለሰቦች ተያዙ

በርካታ አገራት ኮቪድ-19 ምርመራ የሚካሄደው ከአፍንጫ በሚወሰድ ናሙና ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

በኢንዶኔዥያ የሚገኝ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ ሠራተኞች ያገለገሉ የኮቪድ መመርመሪያ መሣሪያዎችን አጥበው ድጋሚ በመሸጥ ወንጀል በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በሜዳን በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ በኩል የተጓጓዙ እስከ 9000 የሚደርሱ መንገደኞች እንደገና ጥቅም ላይ በዋሉት መሣሪያዎች ተመርምረው ሊሆን እንደሚችል ፖሊስ ገልጿል።

በመንግሥት የሚተዳደረው ኪሚያ ፋርማ በተጓዦቹ ስም በተመሠረተ ክስ ፍርድ ቤት ሊቆም እንደሚችል ተዘገቧል፡፡

በኮቪድ ወረርሽኝ በተጠቁ በርካታ አገሮች ውስጥ ከአፍንጫ ፈሳሽ በመውሰድ መመርመር የተለመደ ሆኗል፡፡

ካለፈው ታህሳስ ጀምሮ በሰሜን ሱማትራ ሜዳን በሚገኘው ኳላናሙ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ማጭበርበሩ ሲፈጸም እንደነበር ይታመናል ብሏል ፖሊስ፡፡

ተሳፋሪዎች ለመብረር ከፈለጉ ከተህዋሲው ነጻ መሆን ይጠበቅባቸዋል። አየር ማረፊያው ፈጣን ውጤት ለሚፈልጉ በቦታው የምርመራ አማራጭ ይሰጣል። የአውሮፕላን ማረፊያው ባለሥልጣናት ኪሚያ ፋርማ የሚያቀርበውን አንቲጂን ፈጣን የመመርመሪያ መሣሪያዎችን ይጠቀሙ ነበር ተብሏል፡፡

በስህተት ተህዋሲው እንዳለባቸው የሚያሳይ የምርመራ ውጤት ማግኘታቸውን ተከትሎ ከተሳፋሪዎች ቅሬታ ቀርቧል። ባለፈው ሳምንት ፖሊስ ተሳፋሪ አስመስሎ በህቡዕ መኮንኑን በመላክ ጉዳዩን ማጣራቱን ዴቲክ የተሰኘው የአካባቢው የዜና አውታር ዘግቧል፡፡

ፖሊሱ ከአፍንጫው ናሙናው ተወስዶ ተህዋሲው እንዳለበት ሲነገረው ሌሎች ባልደረቦቹ ወደ ላቦራቶሪው በመግባት እንደገና ጥቅም ላይ የዋሉ የመመርመሪያ መሣሪያ አግኝተዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የሜዳንን ሥራ አስኪያጅ ጨምሮ አምስት የኪሚያ ፋርማ ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከአፍንጫ ናሙና መውሰጃ የጥጥ ዘንጎችን በማጠብ እና በማሸግ ለሽያጭ አቅርበዋል በሚል የጤና እና የሸማቾች ህጎችን በመጣስ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣናት ከ 23 ምስክሮች ሪፖርቶችን አጠናቅረዋል ብለው ዘግበዋል። በጉዳዩ የተጠረጠረው አንዱ ግለሰብ በ124,800 ዶላር ገደማ የገነባው ቅንጡ ቤት ገንዘብ የዚሁ የማጭበርበር የውጤት ስለመሆኑ እየመረመሩ ነው።

መቀመጫውን በዋና መዲናዋ ጃካርታ ያደረገው ኪሚያ ፋርማ በድርጊቱ የተሳተፉ ሠራተኞችን ያባረረ ሲሆን አሠራሩን እንደሚያጠብቅ ቃል ገብቷል፡፡

ባለፉት ወራት በኳላናሙ አውሮፕላን ማረፊያ በተደጋጋሚ በረራ ያደረጉ ሁለት ጠበቆች ኪሚያ ፋራማን ለመክሰስ ማቀዳቸውን የደቡብ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት ዘግቧል፡፡

በጋራ ክስ በመመስረት ለእያንዳንዱ ተጎጂ ተሳፋሪ 1 ቢሊዮን ሩፒያ እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገዋል፡፡

የኢንዶኔዥያ ባለሥልጣናት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በሕንድ የታየው አዲሱ የኮቪድ ዝርያ በሁለት ሰዎች ላይ መገኘቱን ገልጸው ነበር፡፡