ኢትዮጵያ ሱዳን ቤንሻንጉል ክልል ይገባኛል ማለቷ 'ሉዓላዊነትን የሚጻረር ነው' አለች

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

የፎቶው ባለመብት, The Ministry of Foreign Affairs

የምስሉ መግለጫ, አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
ታትሟል

ሱዳን የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚገነባበት ክልል የሆነው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ይገባኛል ማለቷን ኢትዮጵያ አጣጣለች።

የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ የሱዳን መንግሥት ቤንሻንጉል ጉሙዝ ይገባኛል ማለቱን "አስነዋሪ እና ከሕግ ውጪ ነው" ሲሉ አጣጥለውታል።

አምባሳደር ዲና ይህ የሱዳን መግለጫ፤ "የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚጻረር ነው" ብለዋል።

ከቀናት በፊት የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ ፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መጣስ ከቀጠለች ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የይገባኛል ጥያቄ ልታነሳ እንደምትችል አስጠንቅቆ ነበር።

ሱዳን እና ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ለም በሆነው ለእርሻ ተስማሚው አልፋሽቃ የድንበር አካባቢ ይገባኛል በሚል ወታደራዊ ፍጥጫ ውስጥ ከገቡ ወራት ተቆጥረዋል።

ሁለቱ አገራት ተፋጥጠው በሚገኙበት በዚህ የድንበር ይገባኛል ምክንያት ወደ ጦርነት መግባት እንደማይፈልጉ ቢገልፁም የሁለቱ አገራት ሠራዊት ግን በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ መግባታቸው ይሰማል።

ሱዳን በትግራይ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ በአካባቢው ያለው የኢትዮጵያ ጦር ለቅቆ ሲወጣ ስፍራውን መቆጣጠሯ በወቅቱ ተገልጿል።

ከድንበር ውጥረቱ ባለፈም ሱዳን ግብጽ እና ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ላይ የጀመሩት ድርድር አለውጤት መቋጨቱን ተከትሎ በአገራቱ መካከል ያለው ውጥረት ተባብሷል።

አምባሳደር ዲና ማክሰኞ ረፋድ ላይበወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፤ "ሁሉም እንዲረዳው የምንፈልገው ሱዳን በተለይ የኢጋድ ሊቀመንበር ሆና ሳለ፤ ከሕግ ውጪ የሆነ ተግባር መፈጸሟ የሚኮነን እና አሳፋሪ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን" ብለዋል።

አምባሳደር ዲና፤ ሱዳን የኢትዮጵያ መሬት በኃይል ከወረረች በኋላ ያልተገቡ መግለጫዎችን ስታወጣ መቆየቷን ተናግረው፤ ኢትዮጵያ ግን ጉዳዩን በጥሞና ስትከታተል ቆይታለች ብለዋል።

ሱዳን የኢትዮጵያ መሬት በኃይል ከመውረሯም በተጨማሪ ጦሯ ዘረፋ ሲያካሂድ ቆይቷል በማለት የወነጀሉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ጉዳዩን በትዕግስት መመልከቷ እንደ ንቀት ወስዳዋለች ሲሉ አክለዋል።

አምባሳደር ዲና በሁለቱ አገራት መካከል በድንበር ጉዳይ የተከሰተው አለመግባባት፤ ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር እንደማይገናኝ ተናግረዋል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚያሳይ ካርታ

የሶስቱን ሃገራት ድርድር በተመለከተ ኢትዮጵያ ባላት አቋም ጸንታ እንደምትገኝም ገልጸዋል።

ከወራት በፊት በትግራይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ኢትዮጵያ በሱዳን ድንበር ላይ የነበረውን ጦሯን ማንቀሳቀሷን ተከትሎ የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ መያዙን የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም ማስታወቁ ይታወሳል።