በቴክሳስ በአንድ መኖሪያ ቤት 97 ስደተኞች ተደብቀው መገኘታቸው አግራሞትን ፈጠረ

ታትሟል

በቴክሳስ ሂውስተን ከተማ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ 97 ስደተኞች ተደብቀው መገኘታቸው አግራሞትን ፈጥሯል።

ከሜክሲኮ ድንበር በ480 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ መንደር የሚገኙት ነዋሪዎች ፖሊስ በአከባቢያቸው ፍተሻ ካካሄደ በኋላ ስደተኞቹን ማግኘቱ አስደንግጧቸዋል ተብሏል።

በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ተደብቀው ከተገኙ ስደተኞች ጋር በተያያዘ ፖሊስ አምስት ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል።

በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው አምስቱም ሰዎች የደቡብ አሜሪካ አገራት ዜጎች ሲሆኑ በአሜሪካም የተሚኖሩት በሕገ-ወጥ መንገድ ነበር ተብሏል።

ይህ ክስተት ያጋጠመው በ20 አመት ውስጥ ከፍተኛ የስደተኞች ፍሰት በታየበት እና በተለይም የህፃናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በጨመረበት የመጋቢት ወርን ተከትሎ ነው።

የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ ጄኒፈር ሎውሪ ሁሉም ተጠርጣሪዎች "ለንግድ ትርፍ ወይም ለግል የገንዘብ ጥቅም ሲባል ሕገ-ወጥ የውጭ ዜጎችን መጠለያ በመስጠት እና በመደበቅ" ተከሰዋል ብለዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በተጠረጠሩበት ወንጀል ጥፋተኛ ከተባሉ እስከ 10 ዓመት የሚደርስ ቅጣት ሊጣልባቸው ይችላልም ተብሏል።

ስደተኞቹ በሁለት የመኝታ ክፍሎች ውስጥ ወደ ውጪ እንዳይወጡ ተዘግቶባቸው እንደነበረ ተገልጿል። ሁሉም ወንዶች በውስጥ ሱሪያቸው ብቻ ሆነው የተገኙ ሲሆን የተወሰኑት ለሶስት ቀናት ምግብ እና ውሃ አለማግኘታቸውን በመግለጻቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

ከስደተኞቹ ውስጥ እስካሁን አምስቱ የኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው የተረጋገጠ ሲሆን የቀሪዎቹ ውጤት እየተጠበቀ እንደሆነ የሂዩስተን የጤና ጽህፈት ቤት ገልጿል።

ባለስጣናቱ እንዳሉት ለምርመራው ብሎም ስደተኞቹን ለማግኘት ምክንያት የሆነው አንዲት ሴት ወንድሟ እንደታገተ ለፖሊስ በስልክ በማሳወቋ ነው።

ግለሰቧ ወንድሟን ወደ አሜሪካ ለማስገባት 11 ሺህ ዶላር ብትከፍልም ተጨማሪ ካልከፈልሽ እንገልሻለን ሲሉ አዘዋዋሪዎቹ እንዳስፈራሯት መግለጿን ፖሊስ ይፋ አድርጓል።

ፖሊስ የአንደኛውን ተጠርጣሪ የሞባይል ስልክ በመከተል ወደ ቤቱ በማምራት በተደረገ ፍተሻ ስደተኞቹን ማግኘት ችሏል። መርማሪዎች እንዳሉት በቤቱ ውስጥ ከነበሩት ስደተኞች አንዱ ገንዘብ ካልከፈለ "ወደ ሬሳ ሳጥን ውስጥ ነው የምንጨምርህ" ተብያለሁ ሲል ተናግሯል።

በቤቱ ውስጥም ገንዘብ የከፈሉ ሰዎችን ስሞች እና የሂሳብ ድምሮችን የያዘ አንድ ጥራዝ መገኘቱም ተገልጿል።

የቤቱ አከራይም ሆነ ጎረቤቶች ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የተለየ እንቅስቃሴ አይተው እንደማያውቁ እና ቤቱ ምን ላይ ሲውል እንደነበረ እንደማያውቁ ተናግረዋል።