በቡርኪና ፋሶ ታጣቂዎች 30 ሰዎችን ገደሉ

የቡርኪና ፋሶ ጦር በቅኝት ሥራ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቡርኪና ፋሶ ጦር በቅኝት ሥራ ላይ
ታትሟል

ጂሃዲስቶች ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ታጣቂዎች በምስራቃዊ ቡርኪና ፋሶ ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ 30 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ የደህንነት ምንጮች አስታወቁ።

በርካታ ቁጥር ያላቸውና በኃይል የታጠቁ ሰዎች ትናንት ጠዋት ላይ ኮማንጃራ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ኮይዴል መንደር ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ብለዋል ባለስልጣናት።

የደህንነት ምጮች እንዳሉት ቢያንስ 30 ሰዎች በዚህ ጥቃት ተገድለው ከሆነ ይህ ጥቃት በቡርኪና ፋሶ ታሪክ ከፍተኛውን የሰዎችን ሞት ያስመዘገበ ይሆናል።

ቡርኪና ፋሶ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከኒጀር እና ማሊ ጋር በምትዋሰንበት አካባቢ እስላማዊ ታጣቂዎች ጥቃት ማድረሳቸው እየተለመደ የመጣ ነገረ ሆኗል።

በምዕራባዊቷ አገር ከሳምንት በፊት በሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት አደን ላይ የሚሰሩ ሁለት ስፔናውያን እና አንድ አየርላንዳዊ ጋዜጠኞች መገደላቸው የሚታወስ ነው።

"ጠዋት ላይ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው። በወቅቱ አንዳንድ ሰዎች ከቤታቸው እንኳን አልወጡም ነበር'' ብለዋል አንድ ኃላፊ ከኤኤፍፒ የዜና ወኪል ጋር በነበራቸው ቆይታ።

"በአስርታት የሚቆጠሩ ታጣቂዎች በድንገት መንደሪቷን ከበቧትና ቤቶችን በእሳት ማመቃጠል ጀመሩ። ሌሎቹ ታጣቂዎች ደግሞ ቆመው ይመለከቱ ነበር። አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ ሰዎች ተኩስ ከፍተው ነበር"

አንድ ሌላ የሚሊሻ አባል የሟቾችን ቁጥር 30 አካባቢ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን ቁጥሩ ከዚህም በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል ጠቁሟል። "ሰዎች ጥቃቱን ተከትሎ ሲሸሹ ነበር። ከዚህም በላይ ሟቾችን ልናገኝ እንችላለን" ብሏል።

ታጣቂዎቹ በመንደሪቱ ጥቃቱን ያደረሱት በአካባቢው የሚኖሩት የጉርማ ተወላጆች የአካባቢውን ሚሊሻ በመቀላቀላቸው ነው ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት ቡርኪና ፋሶ ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋት ያለባት ሲሆን በሚያዋስኗት ጎረቤት አገራትም ቢሆን ኢስላማዊ አክራሪ ቡድኖች ጥቃቶችን ይፈጽማሉ፤ ሰዎችን አግተው ይወስዳሉ።

በአውሮፓውያኑ 2012 እና 2013 በሰሜናዊ ማሊ የሚገኘውን አካባቢ ታጣቂዎች መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የሳህል ቀጠና ከፍተኛ በሆነ የደህንነት ስጋት ውስጥ ወድቋል።

ፈረንሳይ እና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት በአካባቢው ያለውን የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ወታደሮችን የላኩ ሲሆን እስካሁን ግን እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ማምጣት አልቻሉም።

በዚህ ግጭት ምክንያትም ቢያንስ 3 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።