የጂ7 አገራት 40 ሚሊዮን ሴት ልጆችን ትምህርት ቤት ሊልኩ ነው

የፎቶው ባለመብት, DEA / C. SAPPA
የቡድን ሰባት አገራት በዝቅተኛ እና በመካከለኛ ገቢ ደረጃ ላይ በሚገኙ አገራት የሚኖሩ 40 ሚሊዮን ሴት ልጆችን በቀጣይ አምስት ዓመት ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ከስምምነት ሊደርሱ ነው ተባለ።
አገራቱ በለንደን በሚደረገው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ 15 ቢሊዮን ዶላር በሁለት ዓመት ውስጥ ለማዋጣት ቃል ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከሁለት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ በአካል በሚደረገው በዚሁ ጉባኤ ላይ ተጨማሪ 20 ሚሊዮን ሴት ልጆች በ10 ዓመታቸው ማንበብ እንዲችሉ የሚያስችል ስምምነት ላይ እንዲደርሱም ይጠበቃል።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶሚኒክ ራብ ሴቶችን ማስተማር ብልህ ውሳኔ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ አዲሱ እቅድ ሴት ልጆችን ለተከታታይ 12 ዓመታት ማስተማር ሲሆን ‹‹ሃብት ሁሌም ለጥቂት ሰዎች ሳይሆን ለህብረተሰብ እና ለሃገር መዋል አለበት›› ብለዋል።
አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ ጣሊያን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ጀርመንን የያዘው ቡድኑ ዩኬ ተረኛ ፕሬዘዳንት ስትሆን የዚህን ዓመት ጉባኤም ታስተናግዳች።
ይህ ስምምነት የፊታችን እሮብ ይፈረማል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የአውሮፓ ሕብረትንም ያጠቃልላል ተብሎ ይጠበቃል። ሕብረቱ ከኮቪድ 19 መልሶ ለማገገም በሚል በያዘው እቅድ በመላው አለም የጾታ እኩልነትን የዓለም አቀፍ ተግባራቱ ዋና መሠረት ማድረጉን ማስታወቁ ይወቃል።
የተባበሩት መንግሥታት እንዳስታወቀው ከሆነ በመላው ዓለም ካሉ 796 ሚሊዮን ያልተማሩ ሰዎች ውስጥ ሁለት ሶስተኛው ሴቶች ናቸው።
እንዲሁም 60 በመቶ ከተሜ ወንዶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያገኙ ሲሆን 59 በመቶ ሴቶች ተመሳሳይ እድል አግኝተዋል።
በገጠር 39 በመቶ ሴቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እድል ሲያገኙ ወንዶች 45 በመቶ የመማር እድል አግኝተዋል።












