ኮቪድ-19፡ ሕንድ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎችን አስክሬን ማቃጠያ ቦታ እጥረት ገጠማት

ታትሟል

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በእስያዊቷ አገር ሕንድ ብርቱ ክንዱን አሳርፏል። በቢሊየን የሚቆጠር ሕዝብ በሚኖርባት ሕንድ በየዕለቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኮሮናቫይረስ እንደ ቅጠል እየረገፉ ነው።

ሆስፒታሎች ታማሚዎችን ማከም ከአቅማቸው በላይ ሆኗል። አንድ የታማሚ አልጋ ላይ ሁለት ሰው፣ በረንዳ ላይ፣ መኪና ውስጥ . . . ብቻ በተገኘው ቦታ ኦክስጅን ተገጥሞላቸው ይታያሉ።

ልጅ አባቷን፣ ባል ሚስቱን፣ ሚስት ባሏን፣ ልጅ እናቱን አቅፎ በተሟጠጠ ተስፋ መዳንና መሞትን እኩል ይጠብቃሉ።

ሞታቸው ብቻ ሳይሆን ከሞቱ በኋላ በእምነታቸው መሰረት አስክሬናቸው የሚቃጠልበት ቦታ እጥረትም ያስጨንቃቸው ይዟል።

የሕንዷ ዋና ከተማ ደልሂ ፖሊስ በከተማዋ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኮቪድ-19 ሞት መመዝገቡን ተከትሎ ተጨማሪ የአስክሬን ማቃጠያ ቦታ እንዲዘጋጅ የአካባቢውን ባለሥልጣናት ጠይቋል።

የተወሰነው የሕንድ ክፍል በሁለተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወጀብ እየተናጠ ነው።

በአገሪቷ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች 18 ሚሊየን የደረሰ ሲሆን ሐሙስ ዕለት ብቻ 379 ሺህ 257 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተመዝግቧል። ይህ ቁጥር በሌላው የዓለም አገር ያልታየ በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛው ቁጥር ነው ተብሏል።

ሕንድ ሐሙስ ዕለት ብቻ 3 ሺህ 645 ሰዎችን በሞት አጥታለች። የሞት ቁጥሩ እስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛው መሆኑ ተገልጿል።

ከእነዚህ ውስጥ ከ390 በላይ የሞት ቁጥር የተመዘገበው በዋና መዲናዋ ደልሂ ነው።

ዋና መዲናዋ ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ በአንድ ቀን ይህን ያህል የሞት ቁጥር አጋጥሟት አታውቅም።

የደልሂ የፖሊስ መኮንን "በከተማዋ እያጋጠመ ያለው ሞት በአብዛኛው ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር የተያያዘ ሲሆን ባለው የቦታ እጥረት ሳቢያ ሰዎች በሞት ያጧቸውን ቤተሰቦቻቸውን አስክሬን ለኮቪድ-19 ሟቾች ባልተፈቀደ ቦታ ለማቃጠል ተገደዋል። ለዚህ ነው ተጨማሪ የአስክሬን ማቃጠያ ቦታ መዘጋጀት እንዳለበት የጠየቅነው" ሲሉ መናጋራቸውን ኤንዲቲቪ የዜና አውታር ዘግቧል።

ኦክስጅን፣ መድሃኒት እና የሆስፒታል አልጋዎች እጥረት አጋጥሟል።

ሰዎች የሚወዷቸውን ሰዎች ሊያጡ እንደሆነ በመግለጽ እርዳታ ለማግኘት በማህበራዊ ሚዲያ እየተማፀኑ ነው።

የሕንድ ማዕከላዊ መንግሥት ወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ሳለ፤ የምርጫ ሰልፎች እና ሃይማኖታዊ በዓላት እንዲከበሩ በመፍቀዱ በርካታ ትችቶች እየተሰነዘሩበት ነው።

ይሁን እንጅ የጤና ሚኒስትሩ ሐሙስ ዕለት "በአገሪቷ የተመዘገበው የሞት ቁጥር በዓለም ዝቅተኛው ነው፤ የኦክስጅን አቅርቦቱም 'በቂ' ነው።" ሲሉ በመንግሥት ላይ የቀረበውን ትችት ተከላክለዋል።

ሚኒስትር ሃርሽ ቫርድሃን "ኦክስጅን ከውጭ የሚገባውን ጨምሮ ከተለያዩ ምንጮች እየቀረበ ነው። ማጠራቀሚያውና በዝቅተኛ የሙቀት መጠን የሚያጠራቅመው ታንከር (ክራዮጀኒክ) ተዘጋጅቷል" ሲሉ ለኤኤንአይ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ባለሙያዎች ግን ከዚህ መዓት መውጣት የሚቻለው የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣልና በክትባት ብቻ ነው ብለዋል።

ቅዳሜ ዕለት በሕንድ ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ አዋቂዎች ክትባቱን መውሰድ ይችላሉ ተብሏል። ሕንድ የዓለማችን ትልቋ ክትባት አምራች ብትሆንም ክትባቱን መውሰድ ይችላሉ ለተባሉት 800 ሚሊየን ለሚገመቱ ሰዎች የሚሆን በቂ ክትባት የላትም።

በርካታ አገራትም የክትባት እጥረት እንደገጠማቸው እየተነገረ ነው።

ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎች መኖሪያ በሆነችው የሕንድ የንግድ ማዕከሏ ሙምባይ፤ የቀረበው የክትባት መጠን በማለቁ የክትባት ዘመቻዋን ለሦስት ቀናት ማገዷን አንድ የመንግሥት አካል ያወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የሙምባይ ማዘጋጃ ቤት ኮሚሽነር አሽዊን ቢሃይድ በትዊተር ገጻቸው ላይ፤ ከተማዋ ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች ግን በቂ ክትባት ይኖራታል ብለዋል።