የሳይበር ሰርሳሪዎች የዋሺንግተን ፖሊስ ቢሮ ብዙ ገንዘብ ካልሰጠን ምስጢሩን እንዘረግፋለን ሲሉ ዛቱ

ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, BRENDAN SMIALOWSKI/GETTY IMAGES

ታትሟል

የዋሺንግተን ዲሲ ከተማ የፖሊስ ቢሮ ኮምፒውተሮቹ በሰርሳሪዎች እንደተጠለፈ አስታወቀ።

የኮምፒውተር ሰርሳሪዎች ቡድን በቅጽል ስሙ ባቡክ፣ ፖሊስ በአስቸኳይ ካልተደራደረከኝ ምስጢሩን አደባባይ አሰጠዋለሁ ብሏል።

ሰርሳሪዎቹ ለፖሊስ የሰጡት ቀነ ገደብ 3 ቀናት ብቻ ነው፡፡

የአሜሪካ የምርመራ ቢሮ፣ ኤፍቢአይ፣ የፖሊስ ኮምፒውተር መረጃ የተጠለፈበትን ጥልቀትና ስፋት በመመርመር ላይ ይገኛል፡፡

የኮምፒውተር መረጃ ሰርሳሪዎች ግዙፍ መሥሪያ ቤቶችን መረጃ መረብ በጣጥሰው ከገቡ በኋላ በራሳቸው ቁልፍ ኮምፒውተሮችን ይዘጋሉ፡፡

መረጃ የያዙት ኮምፒውተሮች እንዲከፈቱ የሚሹ ድርጅቶች ለሰርሳሪዎቹ ጠቀም ያለ ገንዘብ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

የዋሺንግተን ፖሊስ ክፍል የገጠመውም ይኸው ነው፡፡

ሰኞ ዕለት የዋሺንግተን ፖሊስ ክፍል አንድ የማያውቀው አካል ኮምፒውተር ትብታቦውን በጣጥሶ ገብቶ መረጃውን እንዳገተበት ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

ባቡክ የሩሲያ ተናጋሪዎች የኮምፒውተር መረጃ ጠላፊ ቡድን በያዝነው የፈረንጆች ዓመት የተከሰተ የኮምፒውተር ሲስተም ወሮበላዎች ቡድን ነው፡፡

አሶሲየትድ ፕሬስ እንደሚለው ቡድኑ ከፖሊስ ክፍል መረጃዎችን በበቂ ሳይዘርፍ አልቀረም፡፡

በቅርቡ በማኅበራዊ የትስስር መረቦች የተሰጣ አንድ የዲጂታል ካርቦን ምስል (ስክሪንሾት) እውነትም ቡድኑ የፖሊስ ምስጢራዊ ደኅንነት ሪፖርቶችን ሳይጠልፍ እንዳልቀረ አመላካች ሆኗል፡፡

ይኸው የዲጂታል ካርቦን ምስል (ስክሪንሾት) በዚህ የጠላፊው ቡድን ድብቅ ድረገጽ ላይም ተለጥፎ ታይቷል፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም መቀመጫውን ያደረገና የበይነ መረብ ደኅንነትን አማክራለሁ የሚል ብሪድዌል ኮንሰልቲንግ ኩባንያ ባልደረባ ጀምስ ስሚዝ እንዳሉት ፖሊስ ለጠላፊዎቹ የጠየቁትን ገንዘብ እንኳ ቢከፍላቸው ምስጢሩ እንደማይሰጣበት እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡

‹‹የፖሊስ መረጃ በብዙ ተባዝቶ ወደ ሌላ ስፍራ ተወስዶ ይሆናል፣ በምስጢራዊ ዘዴ ተጽፎም ለ3ኛ ወገን ተሰጥቶ ይሆናል፣ ስለዚህ መንታፊ ቡድኑን አምኖ የጠየቀውን ገንዘብ መስጠትም አስተማማኝ አይደለም›› ብለዋል ጀምስ ስሚዝ ለቢቢሲ፡፡

ይህ ባቡክ የተባለው አደገኛ የኮምፒውተር መረጃ ጠላፊ ቡድን በቅርቡ የሂውስተን ሮኬትስት ቅርጫት ኳስ ቡድንን የመረጃ ቋት ሰብሮ በመግባት የተጫዋቾችን ውልና የጥቅማ ጥቅም ክፍያ መረጃዎችን በእጁ ማስገባት ችሎ ነበር፡፡

በዚህ ዓመት ብቻ የአሜሪካ መሥሪያ ቤቶች በኮምፒውተር ሰርሳሪዎች 26 ጊዜ የምንተፋ ሙከራ ተደርጎባቸዋል፡፡