በአዲስ አበባ ከሳዑዲ የተመለሱ 'የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ በርካቶች መታሰራቸውን' ቤተሰቦቻቸው ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, facebook
በአዲስ አበባ ከተማ ከሳዑዲ አረቢያ ተመላሾች የሚገኙበት በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች እየታሰሩ እንደሆነ የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ተናገሩ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች በአዲስ አበባ ገላን ኮንደምኒየም እና ሃና ማርያም አካባቢዎች በሚገኙ እስር ቤቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች "በብሔራቸው ምክንያት" እንደታሰሩ ለቢቢሲ ገለፀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ተወላጆች እንደታሰሩ አረጋግጠው፤ ሆኖም ግን በብሔራቸው ምክንያት እንዳልታሰሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑትን አቶ አሮን ማሾን ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ "በትግራይ ተወላጆች ላይ እየተፈፀመ ነው" ስለሚባለው የጅምላ እስር ተጠይቀው ጉዳዩን እያጣሩ እንደሆነና አሁን መረጃ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል።
የታሳሪ ቤተሰቦች በበኩላቸው የታሰሩት የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች፣ የእድሜ ባለፀጋዎች፣ ሴቶች እና ህፃናት እንዲሁም በቅርቡ ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ ስደተኞች እንደሚገኙባቸው ይናገራሉ።
ቢቢሲ ከሳዑዲ አረብያ ተመልሰው በአዲስ አበባ ከተማ ታስረዋል ስለተባሉት የትግራይ ተወላጆች ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆኑትን አምባሳደር ዲና ሙፍቲን ያነጋገረ ሲሆን "በጉዳዩ ላይ መረጃ የለኝም። ግን እዚህ ማንነት ላይ የተነጣጠረ (ኢትኒክ ፕሮፋይሊንግ) ጥቃት የለም። እየተባለ ያለውን ነገር የተፈበረከ ሊሆን ይችላል" የሚል መልስ ሰጥተዋል።
"በተለያዩ ቦታዎች ታስረዋል"
አቶ አብደልቃድር ብርሃኑ፣ ወንድማቸው በአዲስ አበባ ከተማ ገላን ኮንዶሚንየም አካባቢ ከታሰሩት ሰዎች መካከል መሆኑ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"ሰሞኑ ነው ከመቀለ የመጣው፤ ተክለሃይማኖት ከሚባል ቦታ ነው የወሰዱት። አሁን ገላን አካባቢ ከቆርቆሮ በተሰራ እስር ቤት ነው የሚገኘው። ብዙ የትግራይ ልጆች በዚህ ከቆርቆሮ በተሰራ እስር ቤት ታስረው ይገኛሉ። ወንድሜ ለመጠየቅ ሄጄ ነበር፤ ችግር ውስጥ እንዳሉ አይቻለሁ" ይላሉ።
ወንድማቸው ከሌሎች ጋር ተይዞ ከታሰረ ሁለት ሳምንት እንደሆነው የሚገልፁት አቶ ዓብደልቃድር "ከብሔራቸው ውጪ ለመታሰራቸው አንድም ምክንያት የለም" ብለዋል።
የወንድማቸው ጉዳይ እስከ አሁን ወደ ፍርድ ቤት እንዳልቀረበ አክለው ገልጸዋል።
ሌላኛው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሳሙኤል (ስማቸው የተቀየረ) የስኳር በሽታ ታማሚ የሆነው እና በገላን አካባቢ የታሰረውን ጎረቤታቸውን ለመጠየቅ ኢንሱሊን መድኃኒት ይዘው ከታሳሪው ባለቤት ጋር በመሆን መሄዳቸውን ይናገራሉ።
ሆኖም እዚያ እንደደረሱ እስርቤቱ በሚጠብቁ የፀጥታ አካላት እንደተመናጨቁ እና የጤና ችግር ላለባቸው ጎረቤታቸው ያመጡት መድኃኒት በፀጥታ አካላት እንደተጣለ ተናግረዋል።
"ባለቤታቸው በጣም ስለተጨነቀች ይዣት ሄድኩኝ። የስኳር በሽታ ታማሚ ስለሆኑ ኢንሱሊን መድኃኒት ልንሰጣቸው ብንሄድም የሚያስደነግጥ ነገር ነው ያየሁት። ጠባቂዎች ለታሳሪው ባለቤት 'መድኃኒቱን እንዳትሰጪው! ቁጭ በይ!' በማለት አመናጨቋት፤ በጣም አለቀሰች፤ አዘነች። እኔ ሁኔታውን ለማስረዳት ብሞክርም ሂድ! ብለው አመናጨቁኝ። የጤና ችግር ላለበት ሰው የወሰድነውን ኢንሱሊን መድኃኒትም ዐይናችን እያየ ሰባብረው ጣሉት" ይላሉ።
የፀጥታ ኃይሎች በሌሊት መጥተው ጎረቤታቸውን እንደወሰዱዋቸው የሚናገሩት አቶ ሳሙኤል፤ ጎረቤታቸው የታሰሩበት ምክንያት ግልፅ እንዳልሆነ፣ እስከአሁን ቃላቸው ሳይሰጡ እና ወደ ፍርድቤት ሳይቀርቡ ከሳምንት በላይ እንደሆናቸው ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የታሰሩትን የትግራይ ተወላጆች ጉዳይ በቅርበት የሚከታተለውና እንዲፈቱ ጥረት እያደረገ የሚገኘው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ እነዚህ በጅምላ የታሰሩት የትግራይ ተወላጆች በአራት እንደሚከፈሉ ይገልፃል።
"አንድ፤ ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ናቸው። ሁለተኛው በቅርቡ ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ እና በትግራይ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ገና ወደ ትግራይ ሳይሄዱ እዚህ አዲስ አበባ ታፍሰው የታሰሩ ናቸው። ሦስተኛው ደግሞ በከተማዋ በተለያዩ የታችኛው መዋቅር በቀበሌ፣ በክፍለ ከተማና በሌሎች ሲሰሩ የነበሩ ሲሆኑ፣ አራተኛው ምድብ ደግሞ ድንገት በቂም በቀልና በግል ጥላቻ ሰዎች ያሳሰሯቸው ናቸው" ይላል።
በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች የትግራይ ተወላጆች እየታሰሩ እንደሆነ የሚገልፀው ጋዜጠኛ ዳዊት ገላን ኮንዶሚንየም አካባቢ በሚገኘው ከቆርቆሮ በተሰራ መጋዘን ብቻ 736 ያህሉ ታስረው እንደሚገኙ ለቢቢሲ ገልጿል።
"ከእነዚህ ወደ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው፤ 13 በመቶ ደግሞ ሴቶች ናቸው" ብሏል ጋዜጠኛ ዳዊት።
በገላን ታስረው ከነበሩት መካከል ሃና ማርያም (ኦሮሚያ ኮንዶሚንየም አጠገብ) ወደ የሚገኝ መጋዘን የተወሰዱ እንዳሉ የሚገልፀው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ፣ ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ በአውቶብስ የሚመጡ የትግራይ ተወላጆችም ወደ ከተማዋ ከመግባታቸው በፊት ተይዘው በገላን አካባቢ በሚገኘው እስር ቤት እንዲታሰሩ መደረጋቸው ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, Dawit
"ከሳዑዲ እስር ቤት ወደ ኢትዮጵያ እስር ቤት"
በአዲስ አበባ ገላን አካባቢ በመጋዘን ታስረው ከሚገኙት የትግራይ ተወላጆች መካከል በቅርቡ ከሳዑዲ አረቢያ የመጡ ስደተኞች እንደሚገኙበት ይገል ጻል።
የአቶ ኃይላይ (ስማቸው የተቀየረ) አክስት ልጅ በየመን አድርገው ሳዑዲ አረቢያ ከገቡትና ለስድስት ወራት በአሰቃቂ የሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች ታስረው ከነበሩት መካከል አንዱ ነው።
በኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ ወደ ኢትዮጵያ በቅርቡ መግባቱንና በሁለተኛው ቀን በቁጥጥር ስር መዋሉን አቶ ኃይላይ ይገልጻሉ።
"መጋቢት 28/2013 ሐሙስ ቀን ከሳውዲ ወደ ኢትዮጵያ ገባ። አዲስ አበባ እንደገባ ከቀይ መስቀል ወደ ቤት እንድወስደው ወደ ተክለሃይማኖት አካባቢ ወደ እኔ ሲመጣ ቅዳሜ ዕለት ተይዞ ታሰረ።"
ከታሰረ ሁለት ሳምንት እንደሆነው እና ከሳዑዲ አረቢያ መምጣቱ እንደሆነ ለፀጥታ ኃይሎች ቢያስረዱም "ከበላይ አካል ፍቱዋቸው የሚል ትዕዛዝ ካልተሰጠን እኛ የምንሰጣቹ መፍትሄ የለም" መባላቸውን ይናገራሉ።
ከአክስታቸው ልጅ ጋር የታሰሩ ሌሎች አምስት ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ የትግራይ ተወላጆች እንደሚያውቁና ወደ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ለቢቢሲ በሰጠው ቃል "በአሁኑ ሰአት በገላን አካባቢ በሚገኘው እስር ቤት 120፣ በሃና ማርያም 130፤ በአጠቃላይ 250 ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ የትግራይ ተወላጆች ታስረው ይገኛሉ" ብሏል።
አቶ ኃይላይ "ወንድሜ ገና የ30 ዓመት ወጣት ነው። በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት ከባድ ስቃይ አይቷል። ወደ አገር ቤት ሲመለስ መንጃ ፈቃድ ስለነበረው መኪና እያሽከረከረ ህይወቱን ለመምራት እቅድ ነበረው። ይህ ሳይሆን ወደ አገሩ እንደገባ በሁለተኛው ቀን ታሰረ። ከሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት ወደ ኢትዮጵያ እስር ቤት……!" በማለት ገልጿል።
"አገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱትን አስረናል"
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ተወላጆች እንደታሰሩ ለቢቢሲ በማረጋገጥ ሆኖም "በብሔራቸው ምክንያት አልታሰሩም" ይላሉ።
"ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ ሂደው ጦርነቱ አልሳካ ሲላቸው ተመልሰው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የተለያዩ የሽብር ተግባራት የሚፈፅሙና ሕጋዊ ያልሆነ የጦር መሳርያ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ብዙ ሰዎች አሉ። ሁሉንም ካሰርን እስር ቤትም አይበቃም።
"ስለዚህ በዋናነት ለዚህ ተግባር የሚያደራጁ፣ ገንዘብ የሚልኩ፣ ገንዘብ የሚያዋጡ፣ ጦርነቱ እንዳይቆም የተለያዩ ሥራ የሚሰሩና አገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች በተወሰኑ ቦታዎች አስረናል፤ ወደ ፍርድ ቤትም እያቀረብናቸው ነው" ብለዋል።












