ፈረንሳዊያን በጎ ፈቃደኞች ከ40 ቀናት በኋላ ከዋሻ ወጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፈረንሳዊያን በጎ ፈቃደኞች ሰዎች ተገልለው ለምን ያህል ጊዜ ይቆያሉ የሚለውን ለማጥናት 40 ቀናት ዋሻ ውስጥ ከመሸጉ በኋላ ተመልሰዋል።
አስራ አምስቱ በጎ ፈቃደኞች በደቡብ-ምዕራቧ የፈረንሳይ ክፍል ሎምብሪቭስ ለ40 ቀናት መሽገው ከርመዋል።
የጥናቱ ተሳታፊዎች ስልክና ሰዓት ሳይዙ እንዲሁም የፀሐይ ብርሃን ሳያገኛቸው ነው የከረሙት።
በላስቲክ ጎጆ ውስጥ እያደሩ የነበሩት በጎ ፈቃደኞች የራሳቸውን ኮረንቲ በማዘጋጀት ከውጭው ዓለም ጋር ተቆራርጠው ነበር የቆዩት።
ጥናቱ ዓላማ ያደረገው ሰዎች ጊዜ ቆጠራና ያሉበት ሥፍራ ቢጠፋባቸው ምን ይሆናሉ የሚለውን ለመለየት ነው።
ዲፕ ታይም የተሰኘ ስያሜ በተሰጠው በዚህ ጥናት ላይ የተሳተፉ 8 ሴቶችና 7 ወንዶች እሑድ ዕለት ተለቀዋል።
ዕድሜያቸው ከ27-50 የሚመዘዘው የጥናቱ ተሳታፊዎች ዋሻው ውስጥ የነበራቸውን ጊዜ እንዳጠናቀቁ የነገሯቸው ሳይንቲስቶች ናቸው።
ተሳታፊዎች ከዋሻው ሲወጡ ፊታቸው ላይ ፈገግታ ቢነበብም በጭብጨባ የተቀበላቸው ሰው እንደተዳከሙ መለየት አይሳነውም።
ሰዎቹ የፀሐይ ብርሃንን እስኪላመዱ ድረስ በሚል መነፅር እንዲያደርጉ ተደርገው ነበር።
የጥናቱ ኃላፊ የሆኑት ፈረንሳዊ ስዊዙ ክርስቲያን ክሎት እንደሚለው ዋሻው ውስጥ እያሉ ጊዜ በጣም ቀርፋፋ ነበር።
እሱ እንደሚለው ለበርካታ የጥናቱ ተሳታፊዎች "ወደ ዋሻ የመጣን የመሰለን ከ30 ቀናት በፊት ነው።"
ከተሳታፊዎቹ አንዷ የ33 ዓመቷ ማሪና ላንኮን የዋሻው ኑሮ "ሕይወት አንድ ጊዜ ቆማ እንድትጠብቀን እንደማድረግ ነው" ትላለች።
በጥናቱ ወቅት ተሳታፊዎች ጊዜን የሚለኩበት መሣሪያ ሳይኖራቸው ነገር ግን የጊዜ ገደብ ያለው ሥራ እንዲሠሩ ይደረጉ ነበር።
ተሳታፊዎቹ ጊዜን ይለኩ የነበረው ሰውነታቸው በሚሰጣቸው ስሜትና በእንቅልፍ ዑደታቸው ላይ ተንተርሰው ነበር።
በጎ ፈቃደኞቹ በእግር ከሚሽከረከር ብስክሌት መሰል ብረት ነበር ኮረንቲ ሲያመነጩ የነበረው።
ውሃ ደግሞ የሚያገኙት 45 ሜትር ጥልቀት ካለው ጉድጓድ ነበር።
ከጀርባ ያሉ ተመራማሪዎች ጥናቱ ሰዎች በጣም ባልተመቻቸ ሁኔታ ቢኖሩ እንዴት መላመድ እንደሚችሉ ምላሽ የሚሰጥ ነው ይላሉ።
የጥናቱ ተሳታፊዎች ወደ ዋሻው ከመግባታቸው በፊት የአእምሮ ጤናቸውና ጥንካሬያቸው ተልክቶ ነበር።
ጥናቱ በተለይ በኮሮናቫይረስ ዘመን ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ቤታቸው መክረም በተገደዱበት ወቅት ትልቅ ሚና አለው ይላሉ አጥኚዎች።
"በዚህች ምድር ላይ እስካለን ድረስ ነገሮች መቀያየራቸው አይቀርም። ምንም ይሁን ምን ሰዎች በየትኛው ሥፍራ መኖር እንዲችሉ አእምሯቸውን ማለማመድ አለባቸው" ይላሉ የጥናቱ መሪ ክርስቲያን ክሎት።












