በነጆ የወርቅ ማዕድን ማውጫ በተፈጠረ አለመግባባት የሰዎች ህይወት ጠፋ

የፎቶው ባለመብት, EYESWIDEOPEN
በምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ወረዳ በተፈጠረ አለመግባባት የሦስት ሰዎች ህይወት ሲያለፍ ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ተናገሩ።
የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፈ እንደተናገሩት ይህ ክስተት ያጋተመው በነጆ ወረዳ ጉቴ ዲላ ተብላ በምትጠራ ቀበሌ ውስጥ ሲሆን ምክንያቱም በአካባቢው በባህላዊ መንገድ ከሚወጣ የወርቅ ማዕድን ጋር የተያያዘ ነው።
አስተዳዳሪው በአካባቢው ካሉ ከተለያዩ ወረዳዎች የመጡ "ከ7000 በላይ በሕገወጥ መንገድ ወርቅ የሚያወጡ ሰዎች" መኖራቸውን ይናገራሉ።
እነዚህ በሕገወጥ መንገድ ወርቅ የሚያወጡ የሚሏቸው ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ከአምስት ጊዜ ያላነሰ ተደጋጋሚ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ነገር ግን እነዚህ በባህላዊ መንገድ ወርቅ የሚያወጡ ሰዎች "ፍቃደኛ ሆነው ቦታውን ለቀው ለመውጣት ፍቃደኛ አልሆኑም" የሚሉት አቶ ተሊላ ችግሩ የተፈጠረው በድጋሚ ለመወያየት በሄዱበት ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል።
"ለመጨረሻ ጊዜ ልናወያያቸው ወደ ስፍራው ስንሄድ ወደ 5ሺህ የሚገመቱ ሰዎች በአንድ ቦታ ላይ ተሰብስበው ነበር። በዚህ መካከልም ረብሻ ተነሳ" ይላሉ።
አለመግባባቱ በተፈጠረበት ጊዜ ሁኔታውን ለማረጋጋት የመንግሥት ጸጥታ ኃይል በቦታው እንደነበር ገልጸው፤ "የኦነግ- ሸኔ ታጣቂዎችም በስፍራው ይንቀሳቀሳሉ። በዚህ መካከል ተኩስ ተከፍቶ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ ሦስት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል" በማለት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል።
አስተዳዳሪው ለሦስቱ ሰዎች ሞትና ለሌሎች መቁሰል ምክንያት የሆነ ተኩስ ከየትኛው ወገን እንደተተኮሰ ተጠይቀው በሰጡት መልስ "አሁን የምናውቀው ነገር የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ነው። ከየት እንደተተኮስ አላውቅንም" ብለዋል።
በምዕራብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በምዕራብ ወለጋ የምትገኘው የነጆ ወረዳ በወርቅ ማዕድን የምትታወቅ ስትሆን በወረዳው በርካታ ሰዎች ወርቅ በማውጣት ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።
በዚህ ዓመትም ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ መውጣቱን የወረዳው አስተዳዳሪ ይናገራሉ።
"ግለሰቦች እንዳሻቸው የግል መሬታቸውን ይሸጣሉ። ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰዎችም ከሌሎች ስፍራዎች በመኪና ተጭነው ወደ ወርቅ ማውጫ አካባቢው ይመጣሉ" ይላሉ።
የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ እንደሚሉት የማዕድን ማውጫ ስፍራዎቹ "የተለያዩ ወንጀሎችን የፈጸሙ ሰዎች መሰባሰቢያ እየሆነና የሚወጣው ወርቅም ለግል ጥቅም በሕገወጥ መንገድ ለገበያ ይውላል" በማለት ያስረዳሉ።
በዚህ ስፍራ ማዕድን አውጪዎች በባህላዊ መንገድ ወርቅ የሚያወጡ በመሆናቸው የተለያዩ አደጋዎች ሲከሰቱ ይስተዋላል።
ከዚህ ቀደም በነጆ ወረዳ ወርቅ ሲያወጡ በነበሩ ሰዎች ላይ የመሬት መናድ አጋጥሞ ማዕድኑን በማውጣት ላይ የነበሩ ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
መንግሥት የአካባቢው ነዋሪዎች በማኅበር ተደራጅትው ሕጋዊ በሆነ እና ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ወርቅ የማውጣት ሥራ እንዲያከናውኑ ለማድረግ ሲያደርገው የነበረው ጥረት የተፈለገውን ውጤት እስካሁን ማምጣት አለመቻሉን የወረዳው አስተዳዳሪ ተናግረዋል።












