በመድኃኒት እና ኦክስጂን እጥረት ህንዳዊያን እንቅልፍ አጥተዋል

ታትሟል

አኬሂሊሽ ሚሽራ ያለፈው ሐሙስ ነበር ትኩሳት የጀመረው፤ ነገር ግን ጉንፋን ሊሆን ይችላል ብሎ አስቦ ነበር።

በማግስቱ ግን አባቱ ተመሳሳይ ምልክቶችን ማሳየት ሲጀምሩ ነገሩ ያሳስበው ጀመረ። የኮሮናቫይረስ ምርመራ ለማድረግ እና ያልተያዙ የሆስፒታል አልጋዎችን ማፈላለግ ቢጀምርም ከሦስት ቀን ወዲህ አልጋ የሚባል ነገር የለም።

በሚኖሩባት ከተማ እና በዋና ከተማዋ ደልሂ ያሉ የግል ሐኪም ቤቶች መሙላታቸውን እየገለጹ ህሙማንን መመለሳቸውን ቀጥለዋል። በመጨረሻም በደልሂ ያለ አንድ ሆስፒታል ውስጥ አልጋ በመገኘቱ አባት ተኝተው በማገገም ላይ ናቸው።

አኬሂሊሽ አባቱን የሚያጣ መስሎት ነበር። "በጣም ድብርት ውስጥ ገብቼ ነበር፤ ህክምና ሳያገኝ ህይወቱ ያልፍ ይሆናል ብዬም ፈርቼ ነበር። እኔ ባለፍኩበት ጭንቀት ውስጥ ማንም ሰው ማለፍ የለበትም። ሁሉም ሰው እኩል ህክምና የማግኘት እድል ሊኖረው ይገባል" ሲል ይናገራል።

የዚህ ቤተሰብ ታሪክ ከብዙ ህንዳዊያን ታሪክ የሚለይ አይደለም። በመላው ህንድ የሆስፒታል አልጋ ለማግኘት፣ ህይወት የሚያድኑ መድኃኒቶችን እና ኦክስጂን ፍለጋ ብዙዎች እየተንከራተቱ ነው።

መድኒቶች በጥቁር ገበያ

ከቅርብ ግዜ ወዲህ የማኅበራዊ ሚዲያዎችን በተለይ ሬምደሲቪር እና ቶሲሊዙማብ የተሰኙ ሁለት መድኃኒቶችን የሚጠይቁ ሰዎች አጥለቅልቀዋቸዋል።

እነዚህ ሁለት መድኃኒቶች በኮሮናቫይረስ ለተያዘ ሰው የመሰጠታቸው ብሎም ውጤት አላቸው የላቸውም የሚለው በተለያዩ አገራት አከራካሪ ቢሆንም እንደ ህንድ ያሉ አገራት ግን ለድንገተኛ ታማሚዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቅደዋል።

የጸረ ቫይረስ መድኃኒቱ ሬምደሲቪር በመላው ህንድ ባሉ ሐኪሞች እየታዘዘ በመሆኑ ፍላጎቱ ጨምሯል። ህንድ ይህ መድኃኒት ወደ ውጪ እንዳይላክ ብትከለክልም የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ግን ፍላጎቱን ማሟላት ተስኗቸው ትግል ውስጥ ወድቀዋል።

ኤትሮ ፋርማ የተሰኘው እና ይሄንኑ መድኃኒት የሚያመርተው ኩባንያ ምርቱን ለማሳደግ እየሞከረ ነው። ቢቢሲ እንደተረዳው በጥቁር ገበያ ላይ ያለውን ፍላጎት ያባባሰው መድኃኒቶቹ በመደበኛው ገበያ ላይ ያለመገኘታቸው ነው።

ቢቢሲ በደልሂ ያናገራቸው ሦስት ደላሎች አንዷን ባለ 100 ግራም ሬምደሲቪር ጠርሙስ በ320 ዶላር እንደሚሸጡ ገልፀዋል፤ ይህ ከመደበኛ ገበያ አምስት እጥፍ ይልቃል።

የህንድ የጤና ሚኒስቴር ስድስት ጠርሙስ ለአንድ ሰው ህክምና በቂ ነው ቢልም ሐኪሞች ግን አንዳድ ግዜ ስምንት ጠርሙስ የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ሊኖሩ ይችላሉ ይላሉ። ይህ መካከለኛ ገቢ ላለው ሰው ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ነው።

"መድኃኒቱን ለማግኘት ብዙ ገንዘብ ማውጣት ነበረብኝ" ሲል አንድ እናቱ በግል ሆስፒታል ተኝታ የነበረች ህንዳዊ ይናገራል።

ይህንን መድኃኒት ለማግኘትም ብዙ የጭንቀት ሰዓታትን እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ስልኮችን መደወል እንደነበረበት ያስታውሳል።

በተመሳሳይ ቶሲሊ ዙማብ የተሰኘው መድኃኒትም በክሊኒካል ሙከራ የሰው ህይወት ለማዳን እንደሚውል ተረጋጧል። ነገር ግን መድኃኒቱ ከገበያ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሀኔታ ጠፍቷል።

መድኃኒቶች ብቻ ሳይሆኑ የኦክስጅን ፍላጎትም ሰማይ ነክቷል።

ማሃራሽትራ የተሰኘች ግዛት አስተዳዳሪ የፌደራል መንግሥት በጦር አውሮፕላኖች ኦክስጅኖችን በፍጥነት እንዲልክላቸው ጠይቀዋል። በትንንሽ ከተሞች ችግሩ የባሰ ነው።

የሆስፒታል አልጋዎች ባለመኖራቸው የኦክስጂን ሲሊንደር በተገኘበት ሁኑ ታድኖ ከዚያም በህመምተኞች መኖሪያ ቤት መግጠም ብቸኛው አማራጭ ሆኖ ተገኝቷል።

ይህ ብቻ ሳይሆን የግል ሆስፒታሎች ኤክስሬይ ለማንሳት ፈቃደኛ አይደሉም። ሐኪሞች በኮሮናቫይረስ የተያዘ ታካሚያቸውን ሁኔታ ለመገምገም ኤክስሬይ ያዛሉ። አሁን አሁን ኤክስሬይ የሚያነሳ በመጥፋቱ በተለይ በደም ምርመራ ውጤት ላይ ብቻ ተመስረተው ለማከም ተገደዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን የኮሮናቫይረስ እጅግ ባጠቃቸው አካባቢዎች የአስከሬን ማቃጠያዎች እከሚቀልጡ ድረስ ያለ እረፍት እየሰሩ ነው።

ዘመድ አዝማድ የሟች አስከሬንን ለማቃጠል ሰዓታትን መጠበቅ አለበት። እንዲሁም በዚሁ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ያለ እረፍት ቀን እና ለሊት እየሰሩ ነው።

"ቫይረሱ በመጀመሪያ ዙር ሲያጠቃን አልተማርንም። ሁለተኛው ማዕበል እንደሚመጣ እናውቅ ነበር። ነገር ግን እነዚህን አሳዛኝ ነገሮች ለመቀነስ ቀድመን አልተዘጋጀልም። አልጋ፣ ኦክስጂን እና መድኃኒቶች እንዳያጥሩ ማድረግ እንችል ነበር" ሲሉ የወረርሽኝ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ላሊት ተናግረዋል።

"ተመሳሳይ ቀውስ ውስጥ ከገቡ ሌሎች አገራት እንኳን አልተማርንም።"