ኮሮናቫይረስ፡ ዴንማርክ የአስትራዜንካን ክትባት መጠቀም አገደች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ዴንማርክ የኦከስፎርዱን አስትራዜንካ ክትባት መጠቀም እንዳቆመች አስታውቃለች።
ክትባቱ ጋር ተያያይዞ የሚነሳው የደም መርጋት ስጋት እንደፈጠረባት የገለፀችው ዴንማርክ ክትባቱን ሙሉ በሙሉ ላለመጠቀም የወሰነች የመጀመሪያዋ አውሮፓዊት አገር አድርጓታል።
የዴንማርክ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት 2.4 ሚሊዮን መጠን (ዶዝ) ያለው ክትባት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቀመጥ መወሰናቸውን ነው።
የዴንማርክ የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከክትባት ጋር ተያይዞ የሚመጣው የጎንዮሽ የደም መርጋት ችግር ከተጠበቀው በላይ መሆኑን ጥናቶች ማሳየታቸውን ነው።
በጥናቶቹም መሰረት ከ40 ሺህ ሰው አንዱ የክትባቱ የጎንዮሽ ደም መርጋት ችግር ያጋጥመዋል።
የመድኃኒት ቁጥጥርን በበላይነት የሚያየው የአውሮፓ መድኃኒት ኤጀንሲ በባለፈው ሳምንት ክትባቱ የደም መርጋት ሊያመጣ ይችላል የሚል መረጃን ቢሰጥም በኮሮናቫይረስ ታሞ መሞት የበለጠ አስጊ ነው ብሏል።
ከደም መርጋት ጋር በተያየዘ በርካታ የአውሮፓ አገራት አስትራዜንካን አግደውት የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን እድሜያቸው ትልቅ ለሆኑ ሰዎች ክትባቱን በመስጠት ይገኛሉ።
በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ እንዲሁ አሜሪካ፣ ካናዳና የአውሮፓ ህብረት ጆንስን ኤንድ ጆንሰን የተሰኘው ክትባት ከደም መርጋት ጋር በተያያዘ ክትባቱን መጠቀም አቁመዋል።
በደቡብ አፍሪካ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ውጤታማነት አሳይቷል የተባለው ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በደቡብ አፍሪካም ውስጥ ታግዷል።
ለአስትራዜንካም ሆነ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባቶች የደም መርጋት የጎንዮሽ ችግር በጭራሽ አይከሰትም ባይባልም አልፎ አልፎ ታይቷል።
የአውሮፖ ህብረት አባል አገራት የክትባት መርኃ ግብራቸው በአለም ጤና ድርጅት ዘገምተኛ ነው በሚል የተተተቸ ሲሆን ከዚህ በበለጠ የሚዘገይ ከሆነም ቀውሶች ሊከተሉ ይችላሉ ሲል ድርጅቱ አስጠንቅቋል።












