ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ አንድ የቻይና ባለስልጣን የአገሪቱ ክትባቶች ''የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ ነው'' አሉ
አንድ የቻይና ከፍተኛ የበሽታ መቆጣጠር ባለስልጣን ባልተለመደ መልኩ ድክመታቸውን በማመን በአገሪቱ የኮሮናቫይረስ ክትባቶች ውጤታማነት ዝቅተኛ መሆኑን ተናገሩ።
ኃላፊው ጋዎ ፉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ቻይና የክትባቱን ውጤታማነት ለመጨመር ሌሎች ክትባቶችን ለመቀላቀል ማሰቧን አስታውቀዋል።
ቻይና እስካሁን ድረስ በይፋ ጥቅም ላይ የዋሉና ለኅብረተሰቡ የተከፋፈሉ አራት ክትባቶችን ያመረተች ሲሆን፣ ሌሎች አገራት በአንዳንዶቹ ክትባቶች ላይ ባደረጉት ጥናት ውጤታማነታቸው እስከ 50 በመቶ ድረስ ዝቅ ያለ እንደሆነ ገልጸው ነበር።
ነገር ግን ከፍተኛ የበሽታ መቆጣጠር ኃላፊው ይህን ካሉ በኋላ ንግግራቸው ከአውዱ ውጪ መተርጎሙን ገልጸዋል።
ቻይና ውስጥ ከ100 ሚሊየን በላይ ሰዎች ቢያንስ የመጀመሪያውን ዙር ክትባት ወስደዋል።
ቤይጂንግ አሁንም ድረስ ክትባቶቹ ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ ነው፤ እያለች ሲሆን እንደውም ወደ ግዛቴ የሚገቡ የውጭ አገር ዜጎች የቻይና ሰራሽ ክትባት ካልወሰዱ ቪዛ አይሰጣቸውም ብላለች።
የቻይና የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል ዋና ኃላፊው ጋኦ ፉ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ ላይ "በአሁኑ ጊዜ ክትባቶቹ ከፍተኛ የመከላከል ውጤት አላሳዩም’’ ብለዋል።
አክለውም የክትባቶቹን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ክትባቶቹን የመቀላቀል ሃሳብ አቅርበዋል።
ነገር ግን ትንሽ ቆየት ብለው ኃላፊው ንግግራቸውን በማረም ግሎባል ታይምስ ለተባለው መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ "በዓለም ላይ የሚገኙት የኮቪድ-19 ክትባቶች ውጤታማነታቸው አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ ነው አንዳንዴ ደግሞ ዝቅተኛ ነው" ብለዋል።
"የክትባቶቹን ውጤታማነት እንዴት መጨመር ይቻላል የሚለው ጥያቄ በመላው ዓለም በሚገኙ ተመራማሪዎች በሙሉ ከግምት ውስጥ ሊገባ የሚገባው ጉዳይ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።
ቻይና ሰራሽ ክትባቶቹ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ ነው የተባለውም ንግግራቸው ሌላ ትርጉም ተሰጥቶት እንደሆነና ሙሉ በሙሉ የተሳሳተ እንደሆነ ገልጸዋል።
ቻይና እስካሁን ያመረተቻቸው ክትባቶችን በተመለከተ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ብዙም መረጃ ይፋ ያላደረገች ሲሆን በዚህም ምክንያት በክትባቶቹ ውጤታማነት ላይ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል።
ለአብነት ያክል ‘ሲኖቫክ’ የተሰኘው የቻይና ክትባት ብራዚል ውስጥ በተደረገለት ሙከራ 50.4 በመቶ ብቻ ውጤታማነት ያሳየ ሲሆን ይህ ደግሞ በርካቶችን ያሳሳበ ሆኖ ነበር።
በሌላ በኩል ድግሞ ይሄው ሲኖቫክ ክትባት ቱርክ እና ኢንዶኔዢያ ውስጥ ተሞክሮ ውጤታማነቱ 91 በመቶ እና 65 በመቶ መሆኑ ተረጋግጧል።
ቻይና ክትባቶቹን ለሚፈልጉ በሙሉ ለመላክ ፈቃደኛ መሆኗን ያስታወቀች ሲሆን እስካሁንም በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ክትባቶችን እንደ ኢንዶኔዢያ፣ ቱርክ፣ ፖርቹጋል እና ብራዚል ላሉ አገራት ልካለች።