ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቢቢሲ ለልዑል ፊሊፕ ሞት በሰጠው ሰፊ ሽፋን መቶ ሺህ ቅሬታዎችን አስተናገደ
የኤድንብራው መስፍን ልዑል ፊሊፕ ህልፈትን ተከትሎ ቢቢሲ የሰጠው ሽፋን በርካቶች ቅሬታን እንዲያቀርቡ ምክንያት ሆኗል።
ቢቢሲ እስካሁን ድረስ መቶ ሺህ ቅሬታዎችን ማስተናገዱን ዘ ሰን ጋዜጣ ዘግቧል።
ልዑል ፊሊፕ በ99 አመታቸው አረፉ የሚለው ዜና አርብ በተሰማባት እለት ቢቢሲ ያሉትን ፕሮግራሞች ሁሉ አጥፏል።
ኢስት ኢንደርስና ማስተር ሼፍ የተባሉ ፕሮግራሞቹን በልዑሉ ህልፈተ ዜና የተተኩ ሲሆን ቢቢሲ 4 የመሳሰሉ ፕሮግራሞቹ ተሰርዘዋል።
"ለልዑሉ የሰጠውን ሽፋን የምንኮራበት ነው። በዚህ ለአገራችን ቁልፍ በሆነች ዕለት የተጫወትነውም ሚና የሚመሰገን ነው" ብሏል ቢቢሲ በበኩሉ
ሆኖም ምን ያህል ቅሬታዎች ቀርበዋል የሚለው ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ነገር ግን የቀረቡበትን ቅሬታዎች ቁጥር ከሰሞኑ ያስታውቃል።
የልዑሉ የሞት ዜና ሽፋን 100 ሺህ ቅሬታን ማስተናገዱ በቢቢሲ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ወቀሳን ያስተናገደ ሆኖ ተመዝግቧል።
ከዚህ ቀደም 100 ሺህ ባይሞሉም በሽፋናቸው ምክንያት ወቀሳን ካስተናገዱ ዜናዎች መካከል የጄሪ ስፕሪንገር ዘ ኦፔራ የተባለ ፕሮግራሙ 63 ሺህ ቅሬታዎችን እንዲሁም ረስል ብራንድ የተባለው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ለተዋናዩ አንድሪው ሳችስ ለማስደንገጥ ያደረገው ሃሰተኛ የስልክ ጥሪ 42 ሺህ ወቀሳዎችን ተቀብሏል።
ቢቢሲ የልዑሉን ሞት የዜና ሽፋን ለመስጠት በሚል ፕሮግራሞቹን በማጠፉና በመሰረዙ ምክንያት የተመልካቾች ቁጥር ቀንሷል ተብሏል።
ለምሳሌ ያህል አይቲቪ የተባለው የአርብ ምሽት ፕሮግራሙ በመታጠፉ ምክንያት ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር 60 በመቶ የተመልካቾች ቁጥር መውረድ እንዳሳየ መረጃዎች ጠቁመዋል።
የቢቢሲ ዋን ተመልካቾችም ለልዑሉ ሞት በተሰጠው የዜና ሽፋን ምክንያት 6 በመቶ፣ ቢቢሲ ቱ ደግሞ 2/3ኛ ተመልካቾቹን አጥቷል ተብሏል።
በባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ቢቢሲ በሰጠው ሽፋን ምክንያት ለሚቀርቡ ቅሬታዎች ድረ ገፁን ክፍት አድርጎ ነበር።