ብራዚል በአንድ ቀን 4ሺህ ዜጎቿን በኮሮናቫይረስ አጣች

ታትሟል

ብራዚል ለመጀመርያ ጊዜ በ24 ሰዓት 4ሺህ ሰዎች በኮሮና ምክንያት መሞታቸውን ይፋ አደረገች፡፡

ምክንያቱ ደግሞ አዲሱ ዓይነት የኮቪድ ተህዋሲ ዝርያ መከሰቱ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በብራዚል ሆስፒታሎች ከሚችሉት ታማሚ በላይ እያስታመሙ ሲሆን በአንዳንድ ከተሞች ሰዎች አልጋ ወረፋ እየተጠባበቁ ተራ ሳይደርሳቸው ሞት እየቀለባቸው ነው ተብሏል፡፡

የሰው ሰራሽ መተንፈሻ መሣሪያዎች እጥረትም ተከስቷል፡፡

ወረርሽኙ ከመጣ ወዲህ ብራዚል የሞቱባት ዜጎች ቁጥር 337ሺህ የደረሰ ሲሆን ይህም በዓለም ሁለተኛው አስፈሪ ቁጥር ነው፡፡ በዚህን ያህል ቁጥር ዜጎቹ የሞቱበት ከአሜሪካ ሌላ የለም፡፡

በአሜሪካ ከግማሽ ሚሊዮን ዜጎች በላይ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ይህ ሁሉ ዜጋ ሞቶባቸውም ዘጋግቶ ቤት የመቀመጥ እርምጃን ተቃዋሚ ሆነው እንደፀኑ አሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ዜጎች ከቤት እንዳይወጡ ቢደረግ የምጣኔ ሀብት ቀውስና መዘዙ ከኮቪድ-19 የባሰ ሕዝቡን ይጨርሳል፡፡

ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ባለፈው ማክሰኞ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ባደረጉ ጊዜ የእንቅስቃሴ ገደብ ያስቀመጡ የክልል ገዢዎችን ወቅሰዋል፡፡

‹‹ቤት መቀመጥ ትርፉ መወፈርና ድብርት ነው፡፡ ቤት መቀመጥ ትርፉ የሥራ አጥ ቁጥርን ማብዛት ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ንግግራቸው እሳቸው በሚመሯት ብራዚል በ24 ሰዓት 4ሺህ ዜጎች የመሞታቸውን ነገር ሳያነሱ አልፈውታል፡፡

በብራዚል እስከዛሬ በተህዋሲው የተያዙት ሰዎች ቁጥር 13 ሚሊዮን አልፏል፡፡

በደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ብራዚል በመጋቢት ወር ብቻ 66ሺህ ዜጎች ከዚሁ ተህዋሲ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል፡፡