ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኮቪድ-19 መመርያ የጣሰው በ‹ቁጭ-ብድግ› የፖሊስ ቅጣት ሕይወቱ አለፈ
የኮቪድ የእንቅስቃሴ ገደቦችን የጣሰው ፊሊፒናዊ፣ ፖሊስ ስፖርታዊ ቅጣት ጥሎበት ሕይወቱ አለፈ፡፡
ዳረን ማናጎ ፔናሬዶንዶ 12 ሰዓት ከሆነ በኋላ ውሃ ከሱቅ ለመግዛት በወጣበት ነበር ፖሊስ ባለፈው ሐሙስ በቁጥጥር ሥር ያዋለው፡፡
ዳረን የካቫይት አውራጃ ነዋሪ ሲሆን ይህን የሰዓት እላፊና የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣሱ ፖሊስ ቁጭ ብድግ ስፖርት እያሰራው ነበር፡፡ ሆኖም በዚያው አሸልቧል፡፡
በፊሊፒንስ በሉዘን ደሴት የምትገኘው ካቫይት አውራጃ የእንቅስቃሴ ገደብ ታውጆባታል፡፡
የከተማዋ የፖሊስ አዛዥ ማርሎ ሶሌሮ ግን ፖሊሶች የጉልበት ቅጣት እንዲያስፈጽሙ አልነገርናቸውም ብለዋል፡፡
የእንቅስቃሴ ገደቡን የሚጥሱ ሰዎች ምክር ተሰጥቷቸው ነው ወደቤታቸው የሚሄዱት ያሉት ኃላፊው በእርግጥ ፖሊሱ ግለሰቡን ቁጭ ብድግ አሰርቶት ከነበረ ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል፡፡
የሟች ዘመድ አድሪያን ሉሴና የሰውየውን ሞት በፌስቡክ ይፋ አድርጓል፡፡ እሱ እንደገለጸው ዘመዱ ፔናርዶንዶ እና ሌሎች ሰዓት ገደብ ጥሰው የተገኙ ሰዎች ፖሊስ ሰብስቦ 100 ቁጭ ብድግ በኅብረት ሲያሰራቸው ነበር፡፡
በዚህ ቁጭ ብድግ ቅጣት አንድ ሰው ከፎረሸ በድጋሚ ቅጣቱን እንዲደግሙት ይደረግ ነበር፡፡ በዚህም በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰዎች 300 ጊዜ ቁጭ ብድግ እንዲሰሩ ተገደዋል ብሏል፡፡
ሚስተር ፔናሬዶንዶ ሐሙስ ማታ በቁጥጥር ሥር ውሎ አርብ ሌሊት ታሞ ወደ ቤት የመጣ ሲሆን አርብ ቀን ምንም መንቀሳቀስ አቅቶት ውሎ በዚያው አሸልቧል፡፡
በያዝነው ወር መጀመርያ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ሒዩማን ራይትስ ዎች በፊሊፒንስ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ እየተፈጸመ ያለውን ጥብቅ ቅጣትና የሰዎች እንግልት እንዲቆም ጠይቆ ነበር፡፡
ባለፈው ሐሙስ ፕሬዝዳንት ሮድሪጎ ዱቴርቴ በቴሌቪዥን ቀርበው ‹የእንቅስቃሴ ገደቡን የሚጥሱ ዜጎች ወዮላቸው፣ መንገድ ላይ ከተገኙ እኔን አያርገኝ› ሲሉ ለፖሊስ ጥብቅ መመርያን አስተላልፈው ነበር፡፡