ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ብራዚል በመጋቢት ወር ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 ሞተዋል ተባለ
ብራዚል ውስጥ በፈረንጆቹ መጋቢት ወር ብቻ 66 ሺህ 570 ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት መሞታቸውን ከአገሪቱ የወጡ መረጃዎች አመለከቱ።
ይህም ቀደም ካለው የካቲት ወር ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ የጨመረ መሆኑ ተነግሯል።
በአገሪቱ ኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች በጨመረ ቁጥር የጤና ተቋማት አቅም በእጅጉ እየተፈተነ መሆኑን ባለሙያዎች አስረድተዋል።
ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ የተህዋሲውን ወረርሽኝ የያዙበት መንገድ ከፍተኛ ትችት እና ነቀፌታን ያስከተለባቸው ሲሆን በዚህ ሳምንትም አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ሥራውን በገዛ ፈቃዱ ለቋል።
እንዲሁም በአገሪቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ አምስት የጤና ሚኒስትሮች ተቀያይረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ግን አሁንም የተለያዩ ግዛቶች አስተዳዳሪዎች እና ከንቲባዎች በሚያስተዳድሯቸው ከተሞች እና ግዛቶች ውስጥ የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት ያስቀመጡትን የእንቅስቃሴ ገደብ እየተቹ ነው።
"ያለን እና የነበረን ሁለት ጠላት ነው፤ ተህዋሲው እና ሥራ አጥነት! እውነታው ይህ ነው! ይህንን ደግሞ ቤት በመቀመጥ ልንቀርፈው አንችልም" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ብራዚል ረቡዕ ዕለት ተጨማሪ 3 ሺህ 800 ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ሲሞቱ ከ90,000 በላይ አዳዲስ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጣለች።
በብራዚል በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር በዓለማችን በተህዋሲው ምክንያት የሞቱ ሰዎችን አንድ አራተኛ ይይዛል።
የመከላከያ ሚኒስትር ፈርናንዶ አዜቬዶ ኢ ሲልቫን ከስልጣን መነሳት በመቃወም ማክሰኞ ዕለት ከኃላፊነታቸው በለቀቁ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ምትክ ረቡዕ አዲስ የጦር፣ የባሕር እና የአየር ኃይል አዛዦችን ፕሬዝዳንቱ ሾመዋል።
ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ እና ሚኒስትራቸው በጦር ኃይሉ ታማኝነት ዙሪያ አለመግባባት ውስጥ ገብተው እንደነበር ተሰምቷል።
የቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር ጦሩ ታማኝ መሆን ያለበት ለሕገ መንግሥቱ እንጂ የፕሬዝዳነቱን ሰብዕና ለመደገፍ አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል።
ብራዚል ከ21 ዓመታት ወታደራዊ አመራር በኋላ ወደ ዲሞክራሲ ከመጣች ወዲህ የአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የጦር ኃይሉ ሚና በጣም በጥንቃቄ የሚታይ ጉዳይ ነው።
አዲሱ የመከላከያ ሚኒስትር ዋልተር ብራጋ ኔቶ የተለያዩ የጦር ኃይሉን ክፍሎች የሚመሩትን አዲስ ተሿሚዎች አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን እንዲሁም ሌሎች አምስት ሚኒስትሮችንም በአዲስ ተሿሚዎች ተክተዋል።