ኮሮናቫይረስ፡ አሜሪካ "የከፋ ፈተና" ሊገጥማት እንደሚችል ከፍተኛ የጤና ባለሙያ አስጠነቀቁ

ታትሟል

በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ እና ታምመው ወደ ሆስፒታል የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ አገሪቱ "የከፋ ፈተና" ሊገጥማት እንደሚችል አንድ ከፍተኛ ሳይንቲስት አስጠነቀቁ።

ሰኞ ዕለት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተለያዩ ግዛት ፖለቲከኞችን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግን መልሰው እንደ ግዴታ እንዲያስቀምጡ ጥሪ አቅርበው ነበር።

በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይም 90 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን አዋቂዎችም የወረርሽኙን መከላከያ እንደሚከተቡም ቃል ገብተዋል።

አሜሪካ ባለፈው ሳምንት ብቻ 60,000 ያህል ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን በምርመራ አረጋግጣለች።

የአሜሪካ ሕብረተሰብ ጤና ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዶ/ር ሮሼሌ ዋሌኒስኪ በዋይት ሐውስ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ "የከፋ ችግር ሊገጥመን እንደሚችል እየተሰማኝ ስላለው ስሜት አስተያየት መስጠት እፈልጋለሁ" ያሉ ሲሆን አክለውም "ተስፋ ለማድረግ በርካታ ምክንያቶች አሉን ነገር ግን አሁን በጣም ፈርቻለሁ" ብለዋል።

ባለፉት ሳምንታት በቫይረሱ የተያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር በቀን 60 ሺህ ደርሷል።

ዶ/ር ዋሌንስኪ አሜሪካ ዳግም ሌላ የኮቪድ-19 ስርጭት እንድታስመዘግብ አልያም በበርካታ አውሮፓ አገራት እንደሆነው ከፍተኛ ሞትን እንድታይ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

በሚቺጋን እና ኒውዮርክ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፍጥነት እየተስፋፋ ይገኛል።

በቴሌቪዥን ቀርበው ንግግር ያደረጉት ባይደን የግዛት አስተዳዳሪዎች ነዋሪዎቻቸው የአፍ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉ በድጋሚ እንዲያስገድዱ ጠይቀዋል።

በአሜሪካ የኮሮናቫይረስ መከላከያ መመሪያዎች ከግዘት ግዛት ይለያያል።

ባይደን "አሁን መመሪያዎቻችንን ካላላን ቫይረሱ ከመቀነስ ይልቅ ወደ ከፋ ደረጃ ሲሸጋገር እናየዋለን" ብለዋል።

ባይደን አሜሪካ ክትባቱን በማዳረስ ረገድ ያሳያችውን ውጤት በመጥቀስ ከእቅዷ ቀድማለች ብለዋል።

በሚያዚያ ወር ክትባት ለመውሰድ ከሚችሉ አዋቂዎች መካከል 90 በመቶዎቹ ከቤታቸው በቅርብ ርቀት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ባይደን አክለውም በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ሁሉም አዋቂ አሜሪካውያን አንዱን ክትባት ለመውሰድ ይመዘገባሉ ሲሉ እቅዳቸውን ይፋ አድርገዋል።

የአሜሪካ የበሽታዎች መቆጣተሪያ ማዕከል እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ከሆነው መካከል ከአምስት አዋቂ አሜሪካውያን መካከል አንዱ ሙሉ ሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ተከትበዋል ሲል አስታውቋል።

ክትባቱን ለማግኘት የሚችለው ማን ነው? የሚለው ከግዛት ግዛት ይለያያል።

ነገር ግን በሁሉም ግዛቶች በቅድሚያ የጤና ባለሙያዎች፣ ከዚያ በመቀጠል አድሜያቸው ከ65 በላይ ከሆኑት ግለሰቦች ክትባቱን ያገኛሉ።

በጆርጂያ እና አሪዞና ደግሞ እድሜያቸው ከ16 ዓመት በላይ የሆነ ክትባቱን ማግኘት ይችላሉ።

ባይደን አሜሪካውያን አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።