የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራር ምርጫ ያስከተለው ውዝግብ

ታትሟል

ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ወዲህ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ጋር በተያያዘ ውዝግብ መከሰቱ ሲነገር ቆይቶ ሰኞ ዕለት በኮሚቴው ጽህፈት ቤት ውስጥ ተካሄደ የተባለን ስብሰባ ተከትሎ በአካባቢው ተቃውሞ እንደነበር ተሰምቷል።

ይህ በኦሊምፒክ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ደጃፍ የተደረገው የተቃውሞ ሠልፍ የተጠራው የኮሚቴው አባል በሆነው በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንደነበረ የፌዴሬሽኑ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ብስራት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተቃውሞ ሠልፉን ያደረጉበትን ምክንያት ሲያስረዱም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እያደረገ ይገኛል ያሉትን ሕገ ወጥና አግባብ ያልሆነ አሰራርን በመቃወም ነው ብለዋል።

በዚህ ተቃውሞ ላይ በቶኪዮ 2020 ኢትዮጵያን በአትሌቲክ የሚወክሉ አትሌቶች፣ አሰልጣኞች፣ የቀድሞ አትሌቶች፣ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትና የሌሎች አገር አቀፍ የስፖርት ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽን አመራሮች መገኘታቸውን አቶ ስለሺ ጨምረው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም መጋቢት 20/2013 ዓ.ም የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ለማድረግ ከሚገኝበት አቢጃ ኮትዲቯር ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ፤ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውክልና ሳይሰጣቸው በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ ተገኝተዋል ያላቸው ግለሰቦች ላይ እገዳ መጣሉን አሳውቋል።

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮችን ምላሽ ለማካተት ቢቢሲ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ለአሁን አልተሳካለትም።

ነገር ግን ትናንት ማምሻውን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ኮሚቴውን ለቀጣይ አራት ዓመታት እንዲመሩ ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በፕሬዝደንትነት፣ አትሌት ብርሃኔ አደሬ ተቀዳሚ ም/ፕሬዝደንት፣ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው መመረጣቸውን አስፍረዋል።

ቢቢሲ ይህንን መረጃ ከኮሚቴውም ሆነ መመረጣቸው ከተነገረው ሰዎች ለማረጋገጥ አልቻለም።

የሁለቱ አትሌቶች በምርጫው ውስጥ መካተትን በተመለከተ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ ላይ ሂደቱ ሕጋዊ መስመርንና አሰራርን ያልተከተለ ነው በማለት ተቃውሞታል።

ፌዴሬሽኑ በመግለጫው ላይ የኃይሌ ገብረሥላሴና የብርሃኔ አደሬ በኦሎምፒክ ኮሚቴው ከፍተኛ አመራርነት ውስጥ መግባታቸው ለአገር ካበረከቱት አስተዋጽኦ አንፃር ተገቢ መሆኑን ጠቅሶ፤ ነገር ግን "በማኅበር ወይም በፌዴሬሽን የተወከሉ ባለመሆናቸው ህጋዊ መስመሩን ያልተከተለ ነው" ብሏል።

የአሁኑ ውዝግብ መነሻ የሆነው ከዚህ ቀደም አዲስ አመራሮችን መሰየምን በተመለከተ በኮሚቴው የተሰጠው ውሳኔ ባላከበረ ሁኔታ ምርጫ እንዲካሄድ መደረጉ እንደሆነ ይነገራል።

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ ላይ እንደሰፈረውና አቶ ስለሺ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም በታኅሣሥ ወር ሐዋሳ ላይ በተደረገ ጉባኤ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ከቶኪዮ ኦሎምፒክ ማግስት በመስከረም 2014 ዓ.ም ላይ እንዲደረግ መወሰኑን በማስታወስ፣ ይህንን የጣሰ ተግባር በኮሚቴው መፈፀሙን ይናገራሉ።

እንደ አቶ ስለሺ ከሆነ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ይህንን ስምምነት መጣሱ ብቻ ሳይሆን የዓለም ዓቀፉን ኦሎምፒክ ቻርተር እየተገበረ አይደለም ሲሉም ይከሳሉ።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለአባልነት የትምህርት ዝግጅት እንደመስፈርት ማስቀመጡን በተጨማሪም የኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራር በተለይም ፕሬዝዳንቱ የስልጣን ዘመናቸው ስምንት ዓመት እንዲሆን መደረጉንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በቻርተሩ አንድ ግለሰብ ለመመረጥ የትምህርት ዝግጅት እንዲኖረው ማድረጉ ለአባልነት እና ለሥራ አስፈፋሚነት አስፈላጊ አይደለም በማለት ይከራከራሉ።

በዚህም የተነሳ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አባላት ይህ አሰራር መስተካከል አለበት የሚል አቋም እንዳላቸውና ይሀንንም አቋም ሌሎቹ ፌዴሬሽኖች እንደሚጋሩት ይገልጻሉ።

የኦሎምፒክ ኮሚቴ ሰሞኑን በባሕር ዳር ከተማ ተሰብስቦ ምርጫ ለማከናወን ቢሞከርም ፈቃድ ባለማግኘቱ ወደ ሐዋሳ መሻገሩን እዚያም ፈቃድ ባለማግኘታቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሰኞ መጋቢት 20/2013 ዓ.ም ኦሎምፒክ ኮሚቴ ቅጥር ግቢ ውስጥ ምርጫ አደርገው መጠናቀቁ ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም 13 የስፖርት አገር አቀፍ የስፖርት ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች ተቃውሟቸውን ለዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት በጽሁፍ ማሳወቃቸው በማስታወስ ምላሽ እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃም የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን እንዲሁም ባህልና ቱሪዝም ሁለቱ አካላት በጉዳዩ ላይ በጋራ ውይይት ይኖራቸዋል በማለት ሁለቱን አካላት አቀራርቦ በማወያየት ውሳኔያቸውን እንደሚጠበቅ ይናገራሉ።

ይህንን የኦሎምፒክ ኮሚቴ ምርጫን በመቃወምም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አሰልጣኞች ማኅበር መግለጫ ሰጥተዋል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ጃፓን ቶኪዮ ውስጥ እንዲካሄድ ታቅዶ የነበረው የ2020 የኦሊምፒክ ውድድር በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት በዚህ ዓመት ማብቂያ ላይ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያም በሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ በሚካሄደው የዓለማችን ትልቁ የስፖርት ውድድር ላይ የምትሳታፍ ሲሆን፤ ነገር ግን ይህ በኦሊምፒክ ኮሚቴውና በፌዴሬሽኖች እንዲሁም በማኅበራት መካከል ተከሰተው ውዝግብ በቶሎ መፍትሔ ካላገኘ በአገሪቱ ተሳትፎ ላይ ምን ውጤት እንደሚኖረው ወደፊት የሚታይ ይሆናል።