ፈረንሳይ በባህላዊ መንገድ የሚጋገረውን ዳቦ በቅርስነት ይመዝገብልኝ አለች

ባጌት ዳቦ ሲጋገር

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ባጌት ዳቦ ሲጋገር
ታትሟል

በፈረንሳይ ባጌት ተብሎ የሚጠራው ታዋቂ ዳቦ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብላት ፈረንሳይ ጠየቀች።

በተባበሩት መንግሥታት የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ ነው ይህ ቁመተ ረዥም ዳቦ [ባጌት] እንዲካተት ፈረንሳይ ጥያቄ ያቀረበችው።

በዚህ መዝገብ ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አገራት በጊዜ ሂደት እንዳይጠፉ እውቅናና ጥበቃ እንዲያገኙ የሚፈልጓቸውን ባህላዊ ተግባራት፣ የተለያዩ ክህሎቶችና ሌሎችም የማይዳሰሱ ቅርሶች እንዲመዘገቡላቸው የሚጠይቁበት ነው።

ፕላንቶስኮፕ የተባለው የመረጃ ገጽ እንደሚለው፤ ፈረንሳይ ውስጥ በየዓመቱ ወደ 10 ቢሊዮን ገደማ ባጌት የተባለው የዳቦ አይነት ለምግብነት ይውላል።

ፈረንሳያውያን ከአነስተኛ ዳቦ ቤቶች ባጌት መግዛት አቁመው ወደ ትልልቅ መደብሮች በመዛወራቸው ምክንያት፤ እአአ ከ1970 ወዲህ 20,000 የሚደርሱ ዳቦ ቤቶች ተዘግተዋል።

እነዚህ ትልልቅ መደብሮች ግን ዳቦውን የሚጋግሩት ባህላዊውን መንገድ ተከትለው አይደለም።

ባጌት ቅርስ ሆኖ ከተመዘገበ ዳቦው የሚዘጋጅበት ባህላዊ ሂደት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገር እንደሚረዳ የፈረንሳይ ዳቦ ጋጋሪዎች ተስፋ አድርገዋል።

ባጌት የዓለም ቅርስ ተብሎ ከተመዘገበ የአዘገጃጀት ሂደቱ በመዝባሪዎች እንዳይሰረቅ ጥበቃ ይደረግለታል።

ስምንት ዳቦ ቤት ያለው ሚካኤል ሬይድሌት ለሮይተርስ እንደተናገረው፤ "ቅርስ ተብሎ ሲመዘገብ ዳቦ ጋጋሪዎችን እና ቀጣዩን ትውልድም ያበረታታል።"

ፈረንሳይ ውስጥ በባህላዊ መንገድ ይጋገሩ የነበሩ የዳቦ አይነቶች ቀርተው፤ በመደብሮች በጅምላ በሚዘጋጁ ዳቦዎች ተተክተዋል የሚል ቅሬታ አለ።

የዳቦ ጋጋሪዎች ፌደሬሽን ፕሬዘዳንት ዶምኒክ አናክት፤ "ልጅ ሱቅ መላክ የሚጀምረው ባጌት በመግዛት ነው። ይህንን ልማድ የመጠበቅ ኃላፊነት አለብን" ሲሉ ለሮይተርስ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ከዚህ በፊት በቅርስነት ከመዘገባቸው መካከል የኢራን እና የካዛኪስታን ዳቦዎች ይጠቀሳሉ።

ፈረንሳይ በቅርስነት ልታስመዘግብ አስባ ከነበረው መካከል በዚንክ የሚሠራ የቤት ጣሪያ እና ቢዮ አርቦይስ የተባለ የወይን ፌስቲቫል ይጠቀሳሉ።

ባጌት የተባለው የዳቦ አይነት እነዚህን ሁለት ቅርሶች በልጦ ነው በተባበሩት መንግሥታት እንዲመዘገብ የቀረበው።

ለዚህ ጥያቄ የዩኔስኮ ውሳኔ ይፋ የሚሆነው በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ላይ ነው።

ከዚህ ቀደም የደቡብ ኮርያ የፋኖስ ፌስቲቫል፣ የፊንላንድ የሳውና ባህል፣ የቦሲኒያ እና ሄርዞጎቪኒያ የሳር አጨዳ ውድድር በቅርስነት ተመዝግበዋል።