የቀድሞው ፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ ሥርዓት ቀብር ተፈጸመ

ታትሟል

የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዝደንት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ ብሔራዊ ሥርዓት ቀብር ተፈጸመ።

የቀድሞ ፕሬዝደንት ብሔራዊ ስርዓት ቀብር የተፈጸመው በሰሜን ምዕራብ ታንዛኒያ በምትገኘው የትውልድ ቀያቸው ቻቶ ነው።

ታንዛናዊያን የቀድሞ መሪያቸውን በተለያዩ ስፍራዎች ከተሰናበቱ በኋላ ማጉፉሊ ስርዓት ቀብራቸው ዛሬ ተፈጽሟል።

ማጉፉሊ ለሦስት ሳምንታት ያክል ከሕዝብ እይታ ተሰውረው ከቆዩ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ሕልፈተ ህይወታቸው ተሰምቷል።

ማጉፉሊ ባለፉት ጥቂት ወራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ የፕሬዝደንቱ ስም ተያይዞ ሲነሳ ቆይቷል።

ማጉፉሊ፤ 'ኮሮናቫይረስ የለም'፣ 'ክትባት ሳይሆን ጸሎት ነው የሚያስፈልገው' የሚሉ አከራካሪ አስተያየቶችን ሲሰጡ ቆይተዋል።

ኮሮናቫይረስ በታንዛኒያ ሪፖርት ሲደረግ ማጉፉሊ ሕዝቡ ቀን ተሌት እንዲሠራ እንጂ ቤቱ እንዲቀመጥ በፍጹም አይፈልጉም ነበር። ከሰኔ 2020 ጀምሮም ማጉፉሊ አገሬ ታንዛኒያ ከኮቪድ-19 ተህዋሲ ነጻ ነች ሲሉ አወጀውም ነበር።

ማጉፉሊ ጤናቸው ታውኮ ከሕዝብ እይታ በተሰወሩበት ወቅት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ፕሬዝደንቱ በኮቪድ-19 መያዛቸው ሲናገሩ ነበር።

የታንዛኒያ መንግሥት ለፕሬዝደንቱ ሞት ምክንያቱ ከልብ ጋር የተያያዘ የጤና እክል መሆኑን ተናግሮ ነበር።