የትዊተር ፈጣሪ የመጀመሪያ ትዊት 117 ሚሊዮን ብር ተሸጠ

ታትሟል

ትዊተር የተሰኘው ማሕበራዊ ድር አምባ ፈጣሪ የሆነው ጃክ ዶርዚ የመጀመሪያ ትዊት በ2.9 ሚሊዮን ዶላር [117 ሚሊዮን ብር ገደማ] ተሸጠ።

ትዊቱን የገዛው ማሌዢያ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሃብታም እንደሆነ ተጠቁሟል።

የመጀመሪያው መልዕክት "ትዊተሬን እያዘጋጀሁ እገኛለሁ" የሚል ሲሆን የተለጠፈው በፈረንጆቹ መጋቢት 21/2006 ነበር።

ዶርዚ ይህንን ትዊት ለጨረታ ያቀረበው ገቢውን ለእርዳታ ለማዋል በማሰብ ነው።

መቀመጫውን ማሌዢያ ያደረገው ገዥ ሲና ኤስታቪ ትዊቱን መግዛት ማለት የሞና ሊዛን ስዕል እንደመግዛት ነው ሲል አንቆለጳጵሶታል።

ትዊቱ የተገዛው ኤተር በተሰኘው የቢትኮይን ተቀናቃኝ ክሪፕቶከረንሲ ነው።

ትዊቱን ይህን ሁሉ ገንዘብ 'ሆጭ' አድርገው የገዙት ኤስታቪ ብሪጅ ኦራክል የተሰኘው የቴክኖሎጂ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው።

ሰውዬው የንብረት ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጥላቸው 'ኤንኤፍቲ' የተሰኘ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

'ኤንኤፍቲ' ማለት አንድን ፎቶ፣ ቪድዮ አሊያም ሌላ የበይነ-መረብ ይዘት ባለቤትነት የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ነው።

ይህን ወረቀት አባዝቶ ማሠራጨት እጅግ ከባድ ሲሆን እያንዳንዱ ወረቀት ልዩ መለያ አለው።

ዶርዚ የተሰጠውን ክሪፕቶከረንሲ ወደ ቢትኮይን ቀይሮ 'ጊቭ ዳይሬክትሊ' ለተሰኘው የእርዳታ ድርጅት የአፍሪካ ፈንድ ለመስጠት ቃል ገብቷል።

"ይህ ትዊት ብቻ አይደለም" ሲሉ በትዊተር ገፃቸው የፃፉት ገዢው "ሰዎች የዚህ ትዊት ዋጋ የሚገባቸው ወደፊት ነው፤ ልክ እንደ ሞና ሊዛ ስዕል" ብለው ፅፈዋል።

ዶርዚ ትዊቱን የሸጠው በበይነ መረብ ጨረታ ሲሆን ከገቢው 95 በመቶ ወደሱ ኪስ ሲገባ 5 በመቶው ለአጫራቹ ይሰጣል።

ምንም እንኳ ትዊቱ ይሸጥ እንጂ አሁን ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል።