ኮሮናቫይረስ፡ በአሜሪካ የተደረገ ሙከራ የአስትራዜኒካ ኮቪድ-19 ክትባት አስተማማኝ እንደሆነ አረጋገጠ

ታትሟል

አሜሪካ ውስጥ የኦክስፎርድና አስትራዜኒካ ክትባት ላይ የተደረገ ሙከራ ክትባቱ አስተማማኝ እንዲሁም ውጤታማ መሆኑን አረጋገጠ።

በሙከራው ከ32,000 በላይ በጎ ፍቃደኞች የተሳተፉ ሲሆን፤ ክትባቱ 79 በመቶ ያህል የበሽታውን ምልክት በማስወገድ እንዲሁም መቶ በመቶ ሰዎች በቫይረሱ እንዳይያዙ በመከላከል ረገድ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል።

አብዛኞቹ በጎ ፍቃደኞች የተሳተፉት በአሜሪካ ሲሆን ከቺሊ እና ከፔሩ የተሳተፉም አሉ።

ከሙከራው በተገኘ መረጃ መሠረት ክትባቱ የደም መርጋት አያስከትልም።

አስትራዜኒካ የደም መርጋትን የመሰለ የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላል በሚል አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ክትባቱን መስጠት ያቆሙ ሲሆን፤ የሙከራው ውጤት ግን ተስፋ ሰጪ ነው ተብሏል።

በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት የመድኃኒት ተቆጣጣሪዎች ክትባቱ ላይ ሙከራ ካደረጉ በኋላ ክትባቱ እንዲሰጥ ውሳኔ አሳልፈዋል። እነዚህ አገራት የክትባቱን አስተማማኝነት እና ውጤታማነት እንዳረጋገጡ አስታውቀዋል።

በአሜሪካ፤ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ፣ በሮቸስተር ዩኒቨርስቲ እና በአስትራዜኒካ ጥምረት የተካሄደው ሙከራ በርካታ አገራት ክትባቱ ላይ ያላቸውን ጥያቄ ይመልሳል ተብሏል።

በተለይም አረጋውያንን ከቫይረሱ በመከላከል ረገድ ክትባቱ አስተማማኝ እንደሆነም ሙከራው ጠቁሟል።

ብዙ አገራት ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎቻቸው ክትባቱን ላለመስጠት ወስነው ነበር። ይህም ክትባቱ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ መረጃ አላገኘንም በሚል ነበር።

በአሜሪካው ሙከራ ከተሳተፉ በጎ ፍቃደኞች መካከል አንድ አምስተኛ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ነው።

በአራት ሳምንት ልዩነት ሁለት ጊዜ ክትባቱ ተሰጥቷቸው ነው ሙከራው የተካሄደው።

ሙከራው ያስገኘው ውጤት ክትባቱ አሜሪካ ውስጥ በቀጣይ ሁለት ወራት ፍቃድ እንዲሰጠው ያበረታታል ተብሎ ይጠበቃል።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ክትባቱ ላይ የሚደረገውን ምርምር የሚመሩት ፕሮፌሰር አንድሪው ፖላርድ እንዳሉት፤ ከአሜሪካው ሙከራ የተገኘው ውጤት አስደሳች ዜና ነው።

"የሙከራው ውጤት ክትባቱ ለሁሉም እድሜ ክልል አስተማማኝ እንደሆነ ይጠቁማል" ብለዋል።

የክትባት ሥራው መሪ ከሆኑት አንዷ ፕሮፌሰር ሳራ ጊልበርት በበኩላቸው "ክትባቱ በተለያዩ አገራት፣ በተለያየ እድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎችን ከቫይረሱ እንደሚከላከል ታይቷል። ወረርሽኙን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመግታት አጋዥም ነው" ብለዋል።

ክትባት ከወሰዱ በኋላ የሚታመሙ ሰዎች ቢኖሩም፤ ያ ማለት ግን ህመሙ ከክትባቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው ማለት እንዳልሆነ ፕሮፌሰሯ አስረድተዋል።