ራሳቸውን ለመከላከል ከጎልማሳ ጋር የገጠሙት ቻይናዊ አዛውንት አድናቆት ተቸራቸው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአሜሪካ ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል ከጎልማሳ ጋር ግብ ግብ የገጠሙት የ76 ዓመት ቻይናዊ አዛውንት ውዳሴ እየጎረፈላቸው ነው።

ዤ ዢያኦዠን የተባሉት እኝህ አዛውንት በሳንፍራንሲስኮ መንገድ ለመሻገር እየተጠባበቁ ነበር ጎልማሳው መጥቶ በቦክስ የመታቸው።

እርሳቸውም በቅፅበት በእንጨት በትር በመምታት አፀፋ መመለሳቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ በእስያ አሜሪካዊያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እየጨመሩ መሆናቸውን ሪፖርቶች ያሳያሉ።

"አጥቂያቸው ላይ አፀፋ የመለሱት እስያ አሜሪካዊት አዛውንት" የሚለው ዘመቻ በቻይናው ዊቦ ድረ ገጽ በርካታ ተመልካቾችን አግኝቷል። እስካሁንም 1.4 ቢሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል።

በርካቶችም በኦንላይ ለ76 ዓመቷን ዤን አድናቆታቸውን ችረዋል። አንዳንዶች "ጀግና ነች" ሲሉ ሌሎች ደግሞ ይህ ለእነርሱ ትምህርት እንደሆነ በመግለፅ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

በሌላም በኩል በውጭ የሚኖሩ እስያ አሜሪካዊያን በዝምታ ከመሰቃየት አንድ መሆንና ራሳቸውን መከላከል አስፈላጊ መሆኑን ያመላከቱም አሉ።

አንድ የ'ዊቦ' ተጠቃሚ እስያውያን ልዩነት ቢኖራቸውም በአንድ መቆም እንዳለባቸው ጥሪ አቅርቧል።

"ቻይና፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ በጥሩ ወዳጅነት ኖረው አያውቁም። ነገር ግን በአሜሪካ ያላችሁ ሕዝቦች ኃይላችሁ እንዲጠነክር አንድ ሁኑ!" ብለዋል።

"በጣም አሰቃቂ ነበር"

ጥቃቱ የተፈፀመው ረቡዕ ዕለት ነው።

ትውልዷ ጉዋንግዶንግ የሆነችው አዛውንቷ ዤ መንገድ ለማቋረጥ ቆማ እየጠበቁ ነበር።

በዚህም መሃል ነው ድንገት የአንድ ጎልማሳ ቡጢ ዐይናቸው ላይ ያረፈው።

አዛውንቷ ዤ ፊታቸው ላይ በቦክስ ከመመታታቸው በፊት ድንገት አንድ ሰው ' ቻይና ብሎ ሲጣራ መስማታቸውን ይናገራሉ።

ከዚያም በቅፅበት በአቅራቢያቸው ያገኙትን ዱላ አንስተው እንደገጠሙት ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ከጥቃቱ በኋላ የተቀረፀውና በኦንላይን የተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል፤ ዤ ክፉኛ በተጎዳው ዐይናቸው ላይ የበረዶ ከረጢት ይዘው ሲያለቅሱ ያሳያል።

የሳንፍራንሲስኮ ፖሊስ የ39 ዓመቱን ጎልማሳ በቁጥጥር ሥር አውሎ በጥቃቱ ላይ ምርመራ እያካሄደ እንደሆነ አስታውቋል።

የዤ ሴት ልጅ እናቷ ክፉኛ አዕምሯቸው እንደተጎዳና ቀኝ ዐይናቸውም ጉዳት እንደደረሰበት ተናግራለች።

"በጣም ፈርታለች፤ ዐይኗም እስካሁን ይደማል፤ ምንም ነገር ማየትም አትችልም" ስትል ልጃቸው ዶንግ ሜ ሊ ስላሉበት ሁኔታ አስረድታለች።

የልጅ ልጇ ጆን ቼንም ለአያቱ ማሳከሚያ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ 'ጎፈንድሚ' ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።

እርሱ እንደሚለው ከአካላዊ ጉዳታቸው በተጨማሪም የአዕምሮ ጤናቸውም የተረጋጋ አይደለም። የሆነ ነገር ሲባሉ ስሜታዊ መሆንና ለቅሶ ይቀድማቸዋል ብሏል።

ጆን ቼን እስያ አሜሪካዊያን ወጣት ትውልዶች አንዳቸው ለአንዳቸው እንዲሁም ለአረጋውያን መቆም እንዳለባቸው አሳስቧል።

ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ በአሜሪካ ጆርጂያ ግዛት አንድ ግለሰብ ስምንት ሰዎችን በመግደል ክስ ቀርቦበታል። ከስምንቱ ሰዎች መካከል ስድስቱ እስያዊያን ሴቶች ናቸው።

ጥቃቱ በዘረኝነት ሳቢያ የተፈጠረ እንዳልሆነ ቢነገርም ፤ በአሜሪካ የሚኖሩ በርካታ እስያዊያን ግን ስጋት እንደገባቸው ገልጸዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭት የጨመረው በእስያዊያን ላይ ስላለ ነው በሚልም ይወነጀላሉ።

የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ቃል አቀባይ ዣኦ ሊጂያን ሐሙስ ዕለት ባወጡት መግለጫ "በአሜሪካ ቻይናዊያን ላይ የሚደረገው መገለል እየጨመረ ነው" ብለዋል።