የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የተመሳሳይ ፆታ ጥምረትን እንደማትባርክ አስታወቀች

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቄሶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለተመሳሳይ ፆታ ተጣማሪዎች ቡራኬ እንደማትሰጥ የሃይማኖቱን ቀኖና በበላይነት የሚቆጣጠረው የቫቲካን ቢሮ አስታውቋል።

"ለአምላክ ኃጥያትን መባረክ ከባድ ነገር ነው" በማለት የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን አስተምህሮን በመጥቀስ ሰኞ ዕለት ኮንግሪጌሽን ፎር ዘ ዶክትሪን ኦፍ ዘ ፌይዝ (ሲዲኤፍ) የተባለው ቢሮ መልዕክት አስተላልፏል።

ነገር ግን ቢሮው በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ላይ አዎንታዊ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቆም አድርጓል።

በጥቅምት ወር ላይ የሮማው ካቶሊክ ፖፕ ፍራንሲስ የተመሳሳይ ፆታ ጥምረት ሊፈቀድ ይገባል በማለት በአንድ ጥናታዊ ፊልም ላይ ተናግረዋል።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መስረት ጥንዶች የሰርጋቸው ቀን ላይ በካህን ወይም በአገልጋይ ተባርከው ነው ጋብቻቸውን የሚፈፅሙት።

ሰኞ እለት ሲዲኤፍ ያወጣውን ምላሽ ፖፕ ፍራንሲስ ያፀደቁ ሲሆን "ማንኛውንም ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማግለል ላይ ያነጣጠረ አይደለም። ነገር ግን ትክክለኛ የእምነቱ ዶግማና ቀኖና የሚያዘውን ነው የምናደርገው" ብለዋል።

በቅርብ ወራት ውስጥ ጀርመንና አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች አገራት የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያኖች ለተመሳሳይ ፆታ ተጣማሪዎች ቡራኬ እየሰጡ ነው ተብሏል።

ይህም የተመሳሳይ ፆታ ካቶሊክ እምነት ተከታዮችን ወደ ቤተ ክርስቲያኗ እንዲመጡ ለማድረግ እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።

ሲዲኤፍ ይህንን ምላሽ የሰጠው "ቤተ ክርስቲያኗ የተመሳሳይ ፆታ ጥምረት ቡራኬን ትሰጣለች? ወይ የሚል ጥያቄ መቅረቡን ተክትሎ በምላሹም "በፍፁም" ብሏል።

ቤተ ክርስቲያኗ የምታውቀውና የተቀደሰ የምትለው ጋብቻ በሴትና በወንድ መካከል የሚፈፀመውን ነው። ለተመሳሳይ ፆታ ተጣማሪዎች ይህንን እውቅናም ሆነ ቡራኬ አትሰጥም ብሏዕል።

"ቤተ ክርስቲያኗ ከጋብቻ ውጭ የሆነ ወሲብን ያካተተ ማንኛውንም የፍቅር ግንኙነት፣ ጥምረትን፣ አትቀበልም። በሴቶችና በወንዶች ግንኙነት መካከልም ቢሆን ከጋብቻ ውጭ ላለው ግንኙነት ቡራኬ አትሰጥም" ብሏል ባወጣው መግለጫ

ይህንንም ተከትሎ ተራማጅ የሚባሉ የካቶሊክ ቡድኖች በቫቲካን ውሳኔ ላይ ትችታቸውንና ስጋታቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ።

" ቻርሎቴ ክላይመር የተባሉና ካቶሊክ ፎር ቾይዝ የተባለ ድርጅትን ወክለው እንደተናገሩት "የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ምርጫ አይደለም። የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች በአምላክ የተፈጠሩ ፍጥረቶች ናቸው።

ቫቲካንም ይሁን ማንኛውም እምነት ከሚለው በተፃራሪ በዚህ መንገድ ነው የተወለድነው ምንም ስህተት የሌለብን" ብለዋል።

ጌይ ካቶሊክ ግሩፕ የተባለ ቡድን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍራንሲስ ዴ በርናርዶ በበኩላቸው የቫቲካን መግለጫ ባያስደንቃቸውም "ተስፋ አስቆራጭ" ብለውታል።