ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኬንያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን የባሕር ጠረፍ ውዝግብ በሚመለከተው ችሎት አልገኝም አለች
ኬንያ ከሶማሊያ ጋር የገባችበትን የባሕር ጠረፍ ይገባኛል ጥያቄ ጉዳይን ለመመልከት ዛሬ በሚሰየመው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ላይ እንደማትገኝ ቢቢሲ ከአገሪቱ መንግሥት ምንጮች ለማወቅ ችሏል።
ኬንያ በሂደቱ ላይ ላለመሳተፍ የወሰነችው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነው ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ወገንተኝነትን አሳይቷል በሚል ነው።
ኬንያና ሶማሊያ በይገባኛል እየተወዛገቡበት ያለው በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የሚገኝ 160 ሺህ ስኩዌር ኪሎሜትር የሚሸፍን አካባቢ በነዳጅ ዘይትና በተፈጥሮ ጋዝ የበለጸገ ነው ተብሎ ይታሰባል።
ይህ የባሕር ክልል ይገባኛል ጥያቄ በሁለቱ ተጎራባች አገራት መካከል ላለው የዲፕሎማሲ ውዝግብ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።
ኬንያ ጉዳዩን የሚከታተለው አዲስ የሰየመችው ቡድን እስኪዘጋጅና የኮሮናቫይረስ ስጋትን በምክንያትነት በመጥቀስ የችሎቱ ሂደት እንዲዘገይ ብትጠይቅም፤ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ በኢንትርኔት አማካይነት ዛሬ ሰኞ እንዲታይ ወስኗል።
ኬንያ በተጨማሪም ጉዳዩን ከሚመለከቱት ዳኞች መካከል አንድ ሶማሊያዊ መገኘቱን ተቃውማ፤ ግለሰቡ በውሳኔያቸው ላይ የጥቅም ትስስር ስለሚኖር ራሳቸውን ከሂደቱ እንዲያገሉ ጠይቃለች።
ከስድስት ዓመት በፊት ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የወሰደችው ሶማሊያ ስትሆን የባሕር ላይ ጠረፉ በመሬት ላይ ያለውን የሁለቱን አገራት ድንበር በመከተል ወደታች መሰመር አለበት ብላ ትከራከራለች።
ኬንያ በበኩሏ ሁለቱን አገራት የሚለየው የባሕር ጠረፍ በመሬት ላይ ካለው ድንበራቸው በመነሳት ወደታች ሳይሆን ወደጎን መሰመር አለበት በማለት ጥያቄ አንስታለች።
ኬንያ ጉዳዩን እንዲከታተልላት ያዋቀረችው የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ለሚመለከተው ፍርድ ቤት ሥራውን በይፋ ከመጀመሩ በፊት ማብራሪያ ለመስጠት እንደሚፈልግ ገልጾ ነበር።
የኬንያ መንግሥት ከፌደራል መንግሥቱ ፍላጎት በተቃረነ ሁኔታ የጁባላንድ አስተዳደርን በመደገፍ በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እየገባ ነው በሚል ሶማሊያ ትከሳለች።
ሁለቱ አገራት በፖለቲካዊና በድንበር ጉዳዮች ውዝግብ ውስጥ ቢሆኑም የሶማሊያን የተለያዩ አካባቢዎችን የተቆጣጠረውንና በኬንያ ከባድ ጥቃቶችን የፈጸመውን እስላማዊ ቡድን አልሻባብን በመዋጋት በኩል አጋር ናቸው።