ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮቪድ-19 በእንፋሎት ይጠፋል ያሉት ጆን ማጉፉሊ በሽታው ይዟቸው ይሆን?
ለአስራ አንድ ቀናት ያልታዩት የታንዛኒያው ፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ ጉዳይ ጥያቄ እያስነሳ ነው።
ቀንደኛ ተቃዋሚው ቱንዱ ሊሱ 'ምንጮቼ እንደነገሩኝ ከሆነ ፕሬዝደንቱ ኮሮናቫይረስ ይዟቸው ሕክምና ለማግኘት ወደ ኬንያ አምርተዋል' ሲሉ ለቢቢሲ ሹክ ብለዋል።
ነገር ግን ቢቢሲ ይህንን ጉዳዩ ማጣራት አልቻለም።
የማጉፉሊ አስተዳደር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን የመከተበት መንገድ ብዙ ትችት አስተከትሏል።
ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር የኮቪድ-19 ክትባት ላለመግዛት መወሰኗም አነጋጋሪ ነበር።
የ61 ዓመቱ ማጉፉሊ ኮቪድ-19ን ሲያናንቁት ነው የከረሙት። ለዚህ በሽታ ፀሎትና እንፋሎት መታጠን በቂ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
ባለፈው ወር መገባደጃ ገደማ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ቀብር ላይ የተገኙት ማጉፉሊ ታንዛኒያ ኮቪድን ባለፈው ዓመት አሸንፋለች፤ ዘንድሮም ትደግማለች ብለው ነበር።
ባለሥልጣኑ የሞቱት በከፊል ራስ ገዝ የሆነችው የዛንዚባር ደሴት ምክትል ፕሬዝደንት በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወታቸውን ካጡ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።
ተቃዋሚው ሊሱ እንደሚሉት ፕሬዝደንቱ ሰኞ ምሽት ሕክምና ለማግኘት ወደ ናይሮቢ ሆስፒታል አቅንተዋል።
ሊሱ አክለው ፕሬዝደንቱ የልብ ሕመም እንዳጋጠማቸውና አደገኛ ሁኔታ ላእ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
የታንዛኒያ መንግሥት ጆን ማጉፉሊ ከአደባባይ ስለመጥፋታቸው እስካሁን ትንፍሽ ያለው ነገር የለም።
ነገር ግን ለመጨረሻ ጊዜ ከ11 ቀናት በፊት ዳሬ ሳላም ውስጥ ስለታዩት የታንዛኒያው ፕሬዝደንት ያልተረጋገጡ መረጃዎች እንዳይወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
የናይሮቢ ሆስፒታል በበኩሉ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት አልችልም ብሏል።
አቶ ሊሱ መንግሥት ስለ ፕሬዝደንቱ ደህንነት መረጃ አለመስጠቱ ከተማውን ሃሜት እንዲሞላው እያደረገው ነው ይላል።
አክለው የፕሬዝደንቱ ጤና ጉዳይ ግላዊ ምስጢር ሊሆን አይገባም ሲሉ መንግሥትን ይተቻሉ።
የታንዛኒያው ፕሬዝደንት ኮቪድ-19 ቢይዛቸው የሚገርም አይደለም፤ ምክንያቱም ጥንቃቄ ሲያደርጉ አልነበረም ይላሉ ሊሱ።
"የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገው አያውቁም፤ ደግሞ ሕዝብ ወደተሰበሰበበት ያለምንም ጥንቃቄ ይሄዳሉ" ይላሉ በስደት ቤልጂየም የሚገኙት ተቃዋሚው ሊሱ።
"እሳቸው እኮ ለወራት የበሽታውን መድኃኒት ሲያጣጥሉ የከረሙ ናቸው። ፀሎትና ቅጥል ነው የሚያድነው ሲሉ ነበር።"
የ53 ዓመቱ ተቃዋሚ አክለው የፋይንናስ ሚኒስትሩ ፊሊፕ ምፓንጎም በኬንያዋ መዲና ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እያገኙ ነው ይላሉ።
ማጉፉሊ እንደተባለው ኮሮናቫይረስ ይዟቸው ከሆነ አንድም በሽታውን ሲክዱ መኖራቸው ያስተቻቸዋል፤ ሁለት ደግሞ ጎረቤት ሃገር ሄደው መታከማቸው የተደራጀ የጤና ሥርዓት እንደሌለ ማሳያ መሆኑ ያስወርፋቸዋል ትላለች የቢቢሲ አፍሪካ ባልደረባ ለይላ ናቱ።
የታንዛኒያ መንግሥት ኮሮናቫይረስን በተመለከተ መረጃ ስለማይሰጥ የበሽታውን መስፋፋት መጠን መለየት ከባድ ነው።