ፖፕ ፍራንሲስ ታሪካዊ ለተባለው ጉብኝት ለማካሄድ ኢራቅ ገቡ

ጳጳሱን ለመቀበል ባግዳድ አየር ማረፊያ የተገኙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጳጳሱን ለመቀበል ባግዳድ አየር ማረፊያ የተገኙ ሰዎች
ታትሟል

የሮማው ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ታሪካዊ የተባለውን ጉብኝት ለማካሄድ ዛሬ አርብ ኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ ገቡ።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ በኢራቅ የሚያደርጉት ጉብኝት ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ጉዟቸው ነው።

ለአራት ቀናት የሚቆየው ይህ የጳጳሱ ጉብኝት በኢራቅ እየቀነሰ የመጣውን የክርስቲያኑን ሕብረተሰብ ለማነቃቃት ብሎም በተለያዩ ሐይማኖቶች መካከል የሚደረጉ ውይይቶችን ለማበረታታት ያለመ ነው።

በተጨማሪም የካቶሊኩ ጳጳስ በኢራቅ ቆይታቸው እጅግ ከሚከበሩት የሺአ ሙስሊም መሪ ጋር ይገናኛሉ። በሞሱል ከተማ ጸሎት ማድረስ እና በስታዲም ከሕዝብ ጋር መገናኘት ሌሎች ተግባሮቻቸው ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፖፕ ፍራንሲስ በኢራቅ እየጨመረ ያለው የኮሮናቫይረስ ቁጥርም የደኅንነት ስጋት ወደ ኢራቅ ከመጓዝ አላገዳቸውም።

ወደ 10ሺህ የሚጠጉ የኢራቅ ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች የፖፕ ፍራንሲስ ደኅንነትን ለማረጋገጥ የሚሰማሩ ሲሆን በጳጳሱ ጉብኝት ወቅትም የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠር ሰዓት እላፊ ታወጇል።

ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የአሜሪካ ወታደሮች መኖሪያ ካምፕ ላይ የሮኬት ጥቃት ከደረሰ ከሰዓታት በኋላ በሰጡት መግለጫ በኢራቅ ያሉ ክርስቲያኖች "ለሰኮንድም ቢሆን መተው የለባቸውም" ሲሉ ተናግረው ነበር።

እአአ 1991 ዓ.ም የቀድሞው ጳጳስ ጆን ፖል ሁለተኛ በወቅቱ የኢራቅ ፕሬዝዳንት ከነበሩት ሳዳም ሁሴን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ወደ ኢራቅ ሊያደርጉ የነበረውን ጉዞ መሰረዛቸው ይታወሳል።

ከዚያ በኋላ ባሉት ሁለት አስርተ ዓመታት በዓለም ላይ ጥንታዊ ከሚባሉ የክርስቲያን ማኅበረሰብ አንዱ የሆነው የኢራቅ ምዕመናን ቁጥር ከ 1.4 ሚሊዮን ወደ 250 ሺህ ዝቅ ብሏል።

ሳዳም ሁሴንን ያስወገው የአሜሪካ ወረራን ተከተሎም በኢራቅ የክርስቲያን ማኅበረሰቡ ላይ ያተኮሩ ጥቃቶችን በመበራከታቸው ብዙዎች አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትም አይሲስ እኤአ በ2014 የኢራቅን ሰሜናዊ ክፍል መቆጣጠሩን ተከትሎ ከኢራቅ ተሰደዋል።

አይሲስ ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናትን በማፍረስ፣ ንብረታቸውን በመውረስ፣ ግብር እዲከፍሉ በማድረግ፣ ሐይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ማድረግ፣ እንዲሰደዱ ወይም ከሞት ጋር እንዲጋፈጡ ሲያደርግ ቆይቷል።

ይህ የሰሜናዊው ክፍል ወደ 200 ሺህ የሚጠጉት የኢራቅ ክርስቲያኖች መገኛ እንደሆነ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ፖፕ ፍራንሲስ በመጪው እሁድ በሞሱል በሚያደርጉት ጸሎት በአይሲስ የተገደሉ አስር ሺህ ሰዎችን ያስባሉ።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ሙስሊም እና ክርስቲያኖችን አቅፋ የያዘችው የሙሱል ከተማ ዳግም ለማንሰራራት እየጣረች ነው